Fana: At a Speed of Life!

አሜሪካ የህወሓት ታጣቂዎች የፈፀሟቸው የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች፣ የጭካኔ ድርጊቶችና የሲቪል ተቋማት ውድመት እንዳሳሰባት ገለፀች

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 4፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ዪናይትድ ስቴትስ የህወሓት ታጣቂዎች በአማራ እና አፋር ክልሎች በሰላማዊ ሰዎች ላይ ያደረሷቸው የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች፣ የፈፀሟቸው የጭካኔ ድርጊቶች እና በሲቪል ተቋማት ላይ ያደረሷቸው ውድመቶች እንዳሳሰባት ገለፀች።

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ማምሻውን ባወጣው መግለጫ የህወሓት ታጣቂዎች በሁለቱ ክልሎች ሰለፈፀሟቸው እነዚህ የጭካኔ ድርጊቶችን የተመለከቱ ሪፖርቶች አሳስበውኛል ብሏል።

የድርጊቱ ፈፃሚዎች በህግ እንዲጠየቁም መንግስት ምርመራ እንዲያካሂድም ጠይቋል።

የኢፌዴሪ መንግስት አሸባሪው የህወሓት ቡድን በአማራ እና አፋር ክልሎች ወርሮ በያዛቸው አካባቢዎች የፈፀማቸውን ለመናገር የሚከብዱ እጅግ ዘግናኝ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች፣ የጅምላ ጭፍጨፋዎች እና የንብረት ዘረፋና ወድመቶች ዓለም አቀፍ ተቋማት በቦታው በአካል ተገኝተው እንዲመለከቱ ጥሪ ማድረጉ ይታወቃል።

መንግስት ይህንን የህወሓትን የሽብር ተግባር ዓለም አቀፉ ማህበረሠብ እንዲያወግዝም ሲጠይቅ ቆይቷል።

የሽብር ቡድኑ ህወሓት የፈፀማቸውን መጠነ ሰፊ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች፣ የጅምላ ጭፍጨፋዎች እና የሲቪል መሰረተ ልማቶች ውድመት በይፋ ለማውገዝ ዳተኛ ሆና የቆየችው አሜሪካ ድርጊቱን እንድታወግዝ በሀገር ቤት እና በመላው ዓለም የሚገኙ ኢትዬጵያውያን እና ትውልድ ኢትዬጵያውያን በተለያየ መንገድ ሲጠይቁና ግፊት ሲያደርጉም ቆይተዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.