የሀገር ውስጥ ዜና

የመንግሥት ተቋማት የ100 ቀናት ዕቅድ አፈጻጸም ግምገማ ተጀመረ

By Mekoya Hailemariam

December 14, 2021

አዲስ አበባ ፣ ታህሳስ 5 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የፕላን እና ልማት ሚኒስቴር የመንግሥት ተቋማትን የ100 ቀናት ዕቅድ አፈጻጸም መገምገም ጀመረ።

በተመረጡ የልማት ፕሮጀክቶች ላይ የመስክ ምልከታ ጉብኝት ማካሄድ እና መረጃ በመሰብሰብ የተጀመረው ክትትልና ግምገማ፥ በዘርፍ አስፈጻሚ መስሪያ ቤቶች በመገኘት የተቋማቱን የ100 ቀን ዕቅድ አፈጻጸም ደረጃ በዝርዝር ቀርቦ ውይይት ተደርጓል።

ግምገማው የ100 ቀን ዕቅዱን አፈጻጸም በመከታተልና በመገምገም ወጥ እና ጥራቱን የጠበቀ የአፈጻጻም ሪፖርት እንዲዘጋጅ በማድረግ መንግሥት ለሚወስናቸው ውሳኔዎች ግብዓት እንዲሆን ማስቻል ነው፡፡

ከዚህ ባለፈም የ100 ቀን ዕቅድ አፈፃፀም ሪፖርቱ የተሟላ፣ ወቅቱንና ጥራቱን የጠበቀ፣ ወጥ እንዲሆን ማድረግ፣ ድግግሞሽን ማስወገድና የተቀናጀ የዕቅድ አፈፃፀም ሪፖርት እንዲዘጋጅ በማድረግ ተቋማት ለሪፖርት ዝግጅት የሚያጠፉትን የጊዜና የሀብት ብክነት ማስወገድን አላማ ያደረገ ነው ተብሏል።

በየተቋማቱ የተደረገውን ግምገማ ተከትሎ በገምጋሚ ቡድኑ ለተነሱ ጥያቄዎች በየተቋማቱ የስራ ሃላፊዎች ምላሽና ማብራሪያ መሰጠቱን ከፕላን እና ልማት ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።