ቴክ

ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ የኤሌክትሪክ መኪና ባትሪዎች ልታመርት ነው

By Alemayehu Geremew

December 15, 2021

አዲስ አበባ ፣ ታህሳስ 6 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ የኤሌክትሪክ መኪና ባትሪዎች በሀገር ውስጥ ለማምረትና ዕቅድ እንዳላት ተገለጸ፡፡

ኮንጎ በቀጣይ የኤሌክትሪክ መኪኖችን በሀገር ውስጥ ለማምረት ዕቅድ እንዳላትም ነው የሀገሪቷ ፕሬዚዳንት የጠቆሙት ፡፡

የሀገሪቷ ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ጁሊየን ፓሉኩ፥ ሀገራቸው ለባትሪ መሥሪያነት የሚያገለግሉ ማዕድናት ዋና መገኛ መሆኗን ገልጸው፥ የመኪና ባትሪዎችን በሀገር ውስጥ ለማምረት እና በዘርፉ ዕሴት በመጨመር በአረንጓዴ ኢኮኖሚው ላይ የበኩሏን ለመወጣት እንደምትሰራ ነው የገለጹት፡፡

የዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ፕሬዚዳንት ፌሊክስ ሺሲኬዲ፥ ሀገራቸው የኤሌክትሪክ መኪና ገበያውን ለመቀላቀል ቁርጠኛ ሆና እንደምትሠራ ኪንሻሳ በተካሄደው የአፍሪካ ንግድ ፎረም ላይ ገልጸዋል፡፡

ፕሬዚዳንቱ ዕቅዳቸውን ለማሳካትም ከተለያዩ የቴክኒክና የንግድ አጋሮች ጋር በርካታ ሥምምነቶችን እንደተፈራረሙ ነው የተገለጸው፡፡

በአፍሪካ የተባበሩት መንግስታት ኢኮኖሚ ኮሚሽን፣ የአፍሪካ ልማት ባንክ፣ የአፍሪካ ወጪ እና ገቢ ንግድ ባንክ፣ የአፍሪካ የፋይናንስ ትብብር፣ በአፍሪካ የአረብ የኢኮኖሚ እና ልማት ባንክ እንዲሁም የአውስትራሊያ የማዕድን አውጪዎች ቡድን በጉዳዩ ላይ በትብብር ለመሥራት ከፕሬዚዳንቱ ጋር የተፈራረሙ አጋር አካላት እንደሆኑ ዘ አፍሪካ ሪፖርት አመላክቷል፡፡

ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ለመኪና ባትሪ መሥሪያ በዋና ግብዓትነት ጥቅም ላይ የሚውሉ እንደ ሊቲየም፣ ማንጋኒዝ፣ ኒኬል፣ እና ኮባልት ያሉ ማዕድናትን እያወጣች ዕሴት ሳትጨምር ለአሜሪካ እና ለአውሮፓ ገበያ እያቀረበች እንደምትገኝ ይታወቃል፡፡