Fana: At a Speed of Life!

የተመድ ሰብዓዊ መብት ም/ቤት በኢትዮጵያ ላይ የጠራው ልዩ ስብሰባ ገለልተኛ አለመሆኑን እና የፖለቲካ ፍላጎት ማስፈጸሚያ መሆኑን የሚያመላክት ነው – አቶ ከበደ ደሲሳ

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 6፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት በኢትዮጵያ ላይ የጠራው ልዩ ስብሰባ በገለልተኛነቱ ላይ ብዙ ጥያቄችን የሚያስነሳ መሆኑን የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ገለጸ፡፡
 
የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ከበደ ደሲሳ ዛሬ በሰጡት መግለጫ፥ ምክር ቤቱ በኢትዮጵያ ላይ የጠራው ልዩ ስብሰባ ኢትዮጵያ እያከናወነችው ያለውን ስራ ግምት ውስት ያላስገባ እና ያለውን ተጨባጭ ሁኔታ ያላገነዘበ መሆኑን አንስተዋል፡፡
 
የተጠራው ስብሰባ በርካታ ጥያቄችን ያስነሳል ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው÷ ስብሰባው እንዲደረግ ድጋፍ ከሰጡ ሀገራት ውስጥ የአፍሪካ ሀገራት አለመኖራቸው የምክር ቤቱን አድሎዓዊነት በግልጽ ያሳየ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
 
ይህም ችግሩ የአፍሪካውያን መሆኑን ከማረጋገጡ ባለፈ ምክር ቤቱ የአንዳንድ ሀገራት ፖለቲካዊ ፍላጎት ማስፈጸሚ መሆኑን ያረጋገጠ ነው ብለዋል፡፡
 
ከዚህ ባለፈም ውሳኔው ምክር ቤቱን ተዓማኒነት እና ገለልተኝነት ጥያቄ ውስጥ እንደሚስገባም ነው ያነሱት፡፡
 
መንግስት የሰብዓዊ መብት ጥሰት ፈጽሟል ቢባልም እንኳን ምክር ቤቱ አስፈላጊውን አሰራር መከተል እንዳለበት ሚኒስትር ዴታው አስረድተዋል፡፡
 
ከዚህ ባለፈም የኢትዮጵያ መንግስት ተፈጽሟል የተባለውን ችግር በማጣራት እና የማስተካከያ እርምጃ በመውሰድ ላይ ባለበት ሁኔታ ስብሰባው መደረግ አልነበረበትም ነው ያሉት፡፡
 
በሌላ በኩል ምክር ቤቱ አሸባሪው ህወሓት በወረራ ይዟቸው በነበሩ በአማራ እና በአፋር ክልሎች የፈጸመውን ዘግናኝ የሰብዓዊ መብት ጥሰት እና ቁሳዊ ውድመት እንዳልሰማ አልፏል፡፡
 
ይህም ተቋሙ ገለልተኛ አለመሆኑን እና የአንዳንድ ሀገራት ፖለቲካዊ አጀንዳ ማስፈጸሚያ እንደሆነ ያመላክታል ነው ያሉት፡፡
 
ከተመድ የሰብዓዊ መብት ምክር ቤት በተጨማሪም ዩኒስኮ፣ የአለም ጤና ድርጅት እና የመሳሰሉ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች በሽብር ቡድኑ የተፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ማንሳት እንዳማይፈልጉ ጠቁመዋል፡፡
 
ኢትዮጵያ የነዚህን ተቋማት ገልለተኛ ያልሆነ እና መርህን ያልተከተለ አሰራር እና አቋም በጥብቅ እንደምትቃወምም ሚኒስትር ዴኤታው አስገንዝበዋል፡፡
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.