Fana: At a Speed of Life!

አሸባሪው ህወሓት የደሴ ሙዚየምን አውድሞ እና ዘርፎ መሄዱ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 7፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) አሸባሪው የህወሓት ቡድን የደሴ ሙዚየምን አውድሞ እና ዘርፎ መሄዱን የደሴ ከተማ አስተዳደር ባህል ቱሪዝም እና ስፖርት መምሪያ ገለጸ።

የወሎ ሕዝብ የታሪክ፣ የባሕል እና ማንነት መገለጫ የሆኑት ቅርሶች የሚገኙበት የደሴ ሙዚየም በአማራ ክልል ደሴ ከተማ አስተዳደር በአራዳ ክፍለ ከተማ በተለምዶ ዲቪዢን ተብሎ በሚጠራው ሥፍራ ይገኛል።

ሙዚየሙ ከ1973 ዓ.ም በፊት በንጉስ ሚካኤል ቤተ መንግስት ውስጥ ሆኖ የኢትዮጵያ ሕዝብን ባሕል፣ ታሪክ እና ማንነት የሚያሳዩ ሰነዶች ተሰንደውበት ከትውልድ ትውልድ ሲተላለፍ የቆየ መሆኑም የታሪክ ማስረጃዎች አረጋግጠዋል።

ሙዚየሙ በ1973 ዓ.ም በኮለኔል መንግሥቱ ሃይለማሪያም ተመርቆ ሥራ የጀመረ መሆኑንም የከተማ አስተዳደሩ ባህል ቱሪዝም እና ስፖርት መምሪያ ገልጿል።

ሙዚየሙ ቀደም ብሎ የነበረበት ቦታ ለጎብኚዎች ምቹ ሆኖ ባለመገኘቱ አሁን ወደ ሚገኝበት ቦታ እንዲዘዋወር መደረጉንም የደሴ ከተማ አስተዳደር ባህል ቱሪዝም እና ስፖርት መምሪያ አመላክቷል።

የደሴ ሙዚየም የወሎ ሕዝብን፣ አጠቃላይ የአማራ እና የኢትዮጵያ ሕዝብን የዘመናት የታሪክ፣ የባሕል፣ የሥነ ጥበብ ውጤቶች እና ሌሎችም የፈጠራ ሥራዎች የሚገኙበት እንደነበር መምሪያው ገልጾ፥ እነዚህን ተፈጥሮአዊ እና ሰው ሠራሽ ቅርሶችን እና መረጃዎችን የያዘው ሙዚየም በወራሪው ቡድን ተዘርፏል ፤ ወድሟል ብሏል።

በ22 ክፍሎች በተደራጅው የደሴ ሙዚየም ከሚገኙ አስደናቂ እና ማራኪ ቅርሶች መካከል የመጀመሪያው አፄ ምኒልክ ከጅቡቲ እና ከፈረንሳይ መንግስታት ጋር ግንኙነት ያደረጉበት የስልክ ቀፎ፣ በአድዋ ጦርነት ጊዜ ያገለገሉ የተለያዩ የጦር መሣሪያዎች፣ በ1890 ከፈረንሳይ መንግሥት የተበረከተው መድፍ፣ በኢትዮ-ጣልያን ጦርነት ጊዜ በኢትዮጵያዊያን የተማረከው የአየር መቃወሚያ፣ ከ450 ዓመት እድሜ በላይ ያስቆጠሩ የሸክላ ውጤቶች፣ አፄ ምኒልክ በአድዋ ጦርነት ጊዜ በጦር ሜዳ የተጠቀሙባቸው የጦር ሜዳ መነፅሮች፣ እንዲሁም ከብር እና ከወርቅ የተሠሩ ታሪካዊ እና ውድ ቅርሶች ወድመዋል፤ ተዘርፈዋል።

ውድመቱን እና ዝርፊያውን በማስመልከት ለአሚኮ ገለፃ ያደረጉት የደሴ ከተማ አስተዳደር ባሕል ቱሪዝም እና ስፖርት መምሪያ ኀላፊ ሰይድ አራጋው የደሴ ሙዚየም ከብሔራዊ ሙዚየም ቀጥሎ በሁለተኛ ደረጃ የተቋቋመ ሲሆን፥ ሆኖም በወራሪ ቡድኑ ከፍተኛ ውድመት እንደደረሰበት አስታውቀዋል።

አሸባሪ ቡድኑ የአማራ ክልልን እና የኢትዮጵያን ባህል ለማጥፋት የፈጸመው ውድመት መሆኑንም አብራርተዋል።

ዓላማውም የአማራ ክልልን ታሪክ፣ ወግ እና ማንነትን ለማጥፋት ታስቦበት የተሠራ ፤ አማራ ጠልነታቸውን ያሳዩበት ተግባር እንደሆነ ገልጸው፥ በወሎ ባለሃብቶች ተገዝተው የተገጠሙ የሙዚየሙ 26 የደሕንነት ካሜራዎችም ሙሉ በሙሉ መዘረፋቸውን ገልጸዋል።

አካባቢዎን ይጠብቁ!
ወደ ግንባር ይዝመቱ!
መከላከያን ይደግፉ!

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.