Fana: At a Speed of Life!

የኡጋንዳ ብሔራዊ የፓን አፍሪካ ንቅናቄ አስፈፃሚ ሊቀ-መንበር  ለኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት ያላቸውን አጋርነት ገለጹ

አዲስ አበባ ፣ ታህሳስ 7 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በኡጋንዳ የኢፌዴሪ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ዓለምፀሐይ መሰረት በኡጋንዳ ብሔራዊ የፓን አፍሪካ ንቅናቄ አስፈፃሚ ሊቀመንበር ሩጋራማ ዳንኤል ጋር ተወያይተዋል።

የኡጋንዳ ብሔራዊ የፓን አፍሪካ ንቅናቄ አስፈፃሚ ሊቀ-መንበር  ሩጋራማ ዳንኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ወደ ስልጣን ከመጡ ጀምሮ አገራቸውን ሰላማዊ በሆነ መንገድ ለማሻገር ላደረጉት ጥረት እና በዚህ አስቸጋሪ ወቅት እየሰጡት ላለው አመራር አድናቆታቸውን ገልጸዋል።

አጀንዳ 2063ን ለማሳካት እንደ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ያሉ መሪዎች አፍሪካ ያስፈልጓታል ያሉት ሊቀመንበሩ፥ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አፍሪካን ወደፊት ለማራመድ የሚያደርጉትን ጥረት እኛ አፍሪካውያን እየተመለከትነው ነው በዚህም ከጎናቸው ልንቆም ይገባል ብለዋል።

ኢትዮጵያ የአፍሪካ የነፃነት ምልክት፣ በመላው ጥቁር ህዝቦች የአሸናፊነትን ብርሃን የፈነጠቀች፣ ፓን አፍሪካኒዝምን ያቀጣጠለች አገር በመሆኗ የኢትዮጵያ ጉዳይ የአፍሪካውያን ጉዳይ መሆኑንም አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል።

ኢትዮጵያውያን ቅኝ ገዥዎችን በመፋለም እና ድል በማድረግ ለአፍሪካውያን አርዓያ የሆኑ ህዝቦች ናቸው ያሉት ሩጋራማ ዳንኤል፥ በቅኝ ግዛት የነበሩ ሀገራትና ህዝቦችን ነጻ ለማውጣት ኢትዮጵያውያን አብረው መታገላቸውንም አውስተዋል።

አፍሪካውያንም ኢትዮጵያውያን ከዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እየደረሰባቸው ያለውን ጫና ለመቀልበስ በሚያደርጉት ሰላማዊ ትግል የ“#በቃ” ንቅናቄን በመቀላቀል ከጎናቸው የምንቆምበት ጊዜ አሁን ነው ብለዋል።

በመላው ዓለም የሚገኙ ኢትዮጵያውያንም ከመንግስትና ከሀገራቸው ጎን በጽናት በመቆም እያሳዩ ያለውን ሰላማዊ ትግል ታሪክ ይመዘግበዋል፤ ለሌሎች አፍሪካውያን አስተማሪ ሆኖ አልፏልም ነው ያሉት።

አምባሳደር ዓለምፀሐይ መሰረት በበኩላቸው የህወሓት አሸባሪ ቡድን መንግስት የወሰደውን የተናጠል ተኩስ አቁም በመጣስ፥ የአማራና አፋር ክልሎችን በመውረር በንጹኃን ላይ ያደረሰውን ዘግናኝ ግፍ እና ግድያ እንዲሁም ከፍተኛ የመሰረተ ልማት ውድመት በተመለከተ ገለጻ አድርገዋል።

የአገራችንን ወቅታዊ ሁኔታ በተመለከተ በኡጋንዳ የማህበረሰብ አንቂዎች፣ የፓን አፍሪካ ንቅናቄ ተከታዮች እንዲሁም ሚዲያዎች እውነቱን ከማስገንዘብ አንጻር ያላቸው ተሳትፎ ከፍተኛ ነው ማለታቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ፅህፈት ቤት መረጃ ያመላክታል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.