Fana: At a Speed of Life!

የፈጠራ ቅጥፈቶች ለጊዜው ቢያደናግሩም፣ እውነት የመሆን ዐቅም ግን የላቸውም – የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት

አዲስ አበባ ፣ ታህሳስ 8 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የፈጠራ ቅጥፈቶች ለጊዜው ቢያደናግሩም እውነት የመሆን ዐቅም ግን የላቸውም ሲል የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት አስታወቀ።

የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ማምሻውን ባወጣው መግለጫ፥ ኢትዮጵያ የጀመረችው ለውጥ ሰው ተኮርና ለሰዎች መብትና ዕሴት ከፍተኛ ዋጋ የሚሰጥ በመሆኑ የሰብአዊ መብቶች መከበር የብልጽግና ጉዟችን ወሳኝ ጉዳይ ስለሆነ በጀመርነው አቅጣጫ አጠናክረን እንደምንቀጥል ለሕዝባችንና ለወዳጆቻችን እናረጋግጣለን ብሏል፡፡

ከሰሞኑ “በምዕራብ ትግራይ” በዜጎች ላይ የሰብአዊ መብት ጥሰት ተፈጽሟል የሚል የተለመደ፣ የፖለቲካ ፍላጎት ያለበት፣ ለሰሞነኛ ስብሰባ ማድመቂያ የሚውል የፈጠራ ክስ፣ በአንዳንድ የውጭ ሚዲያዎች እየተራገበ እንደሚገኝ የመንግስት መግለጫ ጠቅሶ፥ ይህ የፈጠራ ክስ በተመሳሳይ የይዘት ቅርጽ፣ በተመሳሳይ ጊዜ፣ በተመሳሳይ አገላለጽና አቀራረብ፣ በተለያዩ ቦታዎች በሚገኙ ሚዲያዎች መቅረቡ፣ ነገሩ ፖለቲካዊ ዓላማ ያለው፣ ከአንድ ቦታ ታቅዶ ለሁሉም የተሠራጨ የፈጠራ ክስ መሆኑን እንደሚያሳይ አስረድቷል።

እንዲህ ዓይነቱን ከመርሕና ከሞራል ውጭ የሆነውን ተግባር የኢትዮጵያ መንግሥት በጽኑ እንደሚያወግዘውም አስታውቋል፡፡

አንዳንድ የአሸባሪው አፈ ቀላጤዎች የሆኑ የምዕራብ ሚዲያዎችና አብረዋቸው በሰብአዊ መብት ስም የሚሠሩ ተቋማት በአማራና በአፋር ክልሎች፣ ከጦርነቱ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት በሌላቸው፣ ራሳቸውን መከላከል በማይችሉ ንጹሐን ዜጎች ላይ በማይካድራ፣ ጋሊኮማ፣ ጭና፣ አጋምሳ፣ ውጫሌ፣ አንጾኪያ ገምዛ፣ ኮምቦልቻና ጋሸና በአሸባሪው ሕወሐት የተፈጸሙ ዘግናኝና አሰቃቂ የዘር ጭፍጨፋዎችን ማየትና መስማት እንደማይፈልጉም ነው መግለጫው ያነሳው፡፡

ለኢትዮጵያ መንግሥት የዜጎቹ የሰብአዊ መብት ጉዳይ ቁልፍ አጀንዳ ነው ያለው መግለጫው፥ ይሄንን ሕገ መንግሥታዊ ዕውቅና ያለውን የዜጎችን ሰብአዊ መብት በተሟላ መልኩ ለማስፈጸም ከለውጡ ወዲህ ገለልተኛና ጠንካራ ተቋም መመሥረቱን አስረድቷል፡፡

ከዚህ በፊት ተፈጥረዋል የተባሉ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችንም ከሌሎች ዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር በጋራ በመሆን ሲያጣራ መቆየቱን ገልጾ፥ የምርመራ ግኝቶችንና ምክረ ሐሳቦችን መሠረት አድርጎ ተግባራዊ እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ እንደሚገኝም አብራርቷል።

በዜጎች ላይ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ተፈጽመዋል ከተባሉም የኢትዮጵያ መንግሥት በራሱ የሰብአዊ መብት ተቋማት አማካኝነት እያጣራ፥ በፍትሕ አካላት በኩል ተገቢውን ለማድረግ አሁንም ቁርጠኛ መሆኑንም ነው በአጽንኦት የገለጸው።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.