የሀገር ውስጥ ዜና

ወደ ሀገር ቤት ለሚገቡ እንግዶች አቀባበል የጽዳት ዘመቻ መረሐ-ግብር በይፋ ተጀመረ

By Meseret Awoke

December 18, 2021

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 9፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በቅርቡ ያደረጉትን ጥሪ ምክንያት በማድረግ ወደ ሀገር ቤት ለሚገቡ እንግዶች አቀባበል የጽዳት ዘመቻ መረሐ-ግብር በይፋ ተጀመረ።

እንግዶቹ ወደ አዲስ አበባ ከተማ እስኪገቡ ድረስ ባሉት ተከታታይ ቀናት የሚደረገውን የጽዳት ዘመቻ ዛሬው ከነዋሪዎች ጋር የጽዳት ሥራ በማከናወን በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የከተማ አስተዳደሩ ሥራ አስኪያጅ አቶ ጥራቱ በየነ ዘመቻውን አስጀምረዋል።

የንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍል ከተማ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ነጻነት ዳባ፣ የየካ ክፍለ ከተማ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ይታያል ደጄኔና ሌሎች የከተማና ክ/ከተማ ከፍተኛ የመንግሥት የስራ ኃላፊዎች ተገኝተው የጽዳት ዘመቻውን ከአካባቢው ነዋሪዎች ጋር አከናውነዋል።

በመርሃ ግብሩ ንግግር ያደረጉት ጥራቱ በየነ፥ 1 ሚሊየን ዳያስፖራ ወገኖችን በፍቅር ለመቀበል እና በሚቆዩባቸው ጊዜያት በነፃነት እንዲቆዩ የከተማዋን ሰላም ከማረጋገጥ በተጓዳኝ ውብ፣ ፅዱ እና የምትመች ከተማ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ዳያስፖራው ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት የገና በዓልን እንዲያከብሩ እና የኢትዮጵያን አሁናዊ ሁኔታ እንዲመለከቱ ጥሪ አቅርበዋል።

የየካ ክ/ከተማ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ይታያል ደጄኔ፥ የጽዳት ዘመቻው እንግዶች ወደ መዲናችን አዲስ አበባ እስኪገቡ ድረስ በዘላቂነት የሚከናወን መሆኑን ገልጸዋል።

ጀሞ አደባባይ የተደረገውን የጽዳት ዘመቻ በይፋ ያስጀመሩት የንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ በጽዳት ዘመቻው ላይ እንደተናገሩት፥ የመረሐ -ግብሩ ዓላማ ከውጭ የሚገቡ ወገኖቻችንን ከተማችንን ጽዱ አድርገን ለመቀበል በማሰብና በጋራ ተናበን አገራችንን ለመገንባት ነው ብለዋል።

መገናኛና ጀሞ አደባባይ ተገኝተው የጽዳት ዘመቻውን ያከናወኑ የአካባቢው ነዋሪዎች እንደገለፁት ÷ በሚቀጥሉት ቀናት በተከታታይ በሚደረገው የጽዳት ዘመቻ በንቃት በመሳተፍ ከተማችንንና አካባቢያችንን ከውጭ ለሚገቡ ወገኖቻችንን ጽዱና ማራኪ በመድረግ በሚንቀሳቀሱበት አካባቢ ሁሉ ጥሩ የእረፍት ጊዜ ማሳለፍ እንዲችሉ ለማድረግ እንደሆነ መናገራቸውን ከከተማዋ ፕሬስ ሴክሬታሪ ያገነነው መረጃ ያመለክታል።

አካባቢዎን ይጠብቁ! ወደ ግንባር ይዝመቱ! መከላከያን ይደግፉ!

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!