Fana: At a Speed of Life!

በመተከል ዞን ለውክልና ጦርነት የተሰለፉ ፀረ-ሰላም ሃይሎች ላይ የተጠናከረ እርምጃ ይወሰዳል-አቶ ገዱ

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 10፣ 2014(ኤፍ ቢ ሲ) በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን ለውክልና ጦርነት የተሰለፉ ፀረ-ሰላም ሃይሎች ላይ የተጠናከረ እርምጃ የሚወሰድ መሆኑን የጠቅላይ ሚኒስትሩ የደሕንነት ጉዳዮች አማካሪ አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ተናገሩ።
 
የአካባቢው ማህበረሰብም መንግስት በወንጀለኞች ላይ እየወሰደ ያለውን እርምጃ በመደገፍ ተጠርጣሪዎችን በማጋለጥና ተጠያቂ እንዲሆኑ በማድረግ ትብብራቸው እንዲቀጥል ጠይቀዋል።
 
ለዞኑ የጸጥታ ችግር ዘላቂ እልባት ማበጀት በሚቻልበት ጉዳይ ላይ የአገር ሽማግሌዎችና የጎሳ መሪዎችን ያሳተፈ የሰላም ጉባኤ በግልገል በለስ ከተማ ተካሂዷል።
 
በመርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት የጠቅላይ ሚኒስትሩ የደህንነት አማካሪ አቶ ገዱ አንዳርጋቸው÷ በመተከል ዞን በየጊዜው በሚፈጠር የውክልና ጦርነት በርካታ ንጹሃንን ለሞትና መፈናቀል መዳረጉን ገልጸዋል።
 
በአካባቢው ሰላምና መረጋጋት እንዳይኖር የሚሹ አካላት በሚያቀናብሩት ሴራ የአካባቢው ማህበረሰብ በፀረ ሰላም ሃይሎች በርካታ ችግሮች እየደረሱበት መሆኑንም አንስተዋል።
 
መንግስት ለችግሩ እልባት ለመስጠት የተለያዩ አማራጮችን ቢያቀርብም እስካሁንም በጥፋት መንገዳቸው የቀጠሉ ሃይሎች መኖራቸውን ጠቅሰዋል።
 
በመሆኑም መንግስት የዜጎችን ሰላም ለማስጠበቅ ለሚያደርገው ጥረት የሀገር ሽማግሌዎች፣ የጎሳ መሪዎች እና አጠቃላይ ማህበረሰቡ ከመንግስት ጎን በመቆም ጸረ-ሰላም ሃይሎችን መታገል አለበት ብለዋል።
 
በዞኑ ለውክልና ጦርነት የተሰለፉ ፀረ-ሰላም ሃይሎች ላይ የተጠናከረ እርምጃ እንደሚወሰድም ነው ያረጋገጡት።
 
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አሻድሊ ሀሰን በበኩላቸው÷ በዞኑ የውክልና ጦርነት አጀንዳ አንግበው በተላላኪዎቻቸው በኩል በህዝብ ላይ ከፍተኛ ችግር የሚፈጥሩ የጥፋት ፈፃሚዎች ላይ የተጠናከረ እርምጃ እንወስዳለን ብለዋል።
 
የዞኑ የኮማንድ ፖስት አስተባባሪ ሌተናል ጄነራል ሐሰን ኢብራሂም÷ መንግስት በአካባቢው የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥ የመከላከያ ሠራዊትና የክልል ልዩ የጸጥታ ሃይል በዞኑ ማሰማራቱን ገልፀዋል።
 
በመሆኑም በዞኑ የሚንቀሳቀሱ የጥፋት ሃይሎች እጃቸውን ለመንግስት እንዲሰጡ ጠይቀው፤ እጅ የማይሰጡ ካሉ ግን የማያዳግም እርምጃ ይወሰዳል ብለዋል።
 
የጸጥታ ሃይሉ በወንጀለኞች ላይ ለሚወስደው እርምጃ የአካባቢው ማህበረሰብ ተባባሪ እንዲሆንም ሌተናል ጄነራል ሐሰን መጠየቃቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
 
የውይይቱ ተሳታፊዎችም በዞኑ ዘላቂ ሰላም ለማስፈን መንግስት የሚያደርገውን ጥረት በመደገፍ ጸረ-ሰላም ሃይሎችን ለመዋጋት ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።
 
አካባቢዎን ይጠብቁ!
ወደ ግንባር ይዝመቱ!
መከላከያን ይደግፉ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.