Fana: At a Speed of Life!

ከህልውና ዘመቻው ጎን ለጎን መካከለኛ እና ሰፋፊ የመስኖ ግንባታ ፕሮጀክቶች እየተከናወኑ ነው – መንግስት

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 11፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ከህልውና ዘመቻው ጎን ለጎን መካከለኛ እና ሰፋፊ የመስኖ ግንባታ ፕሮጀክቶች እየተከናወኑ መሆኑን የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ገለጸ፡፡

የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዲኤታ ሰላማዊት ካሳ በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡

በመግለጫቸውም አሸባሪው ህወሓት በተለያዩ አካባቢዎች ላይ ያደረሰው ሰብዓዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጉዳት ከፍተኛ መሆኑ ጠቅሰዋል፡፡

እነዚህ አካባቢዎች አምራች ከመሆናቸው ጋር ተያይዞ ይህን ለማካካስ እና በአገር ላይ የሚደርሰውን ጫና ለመቀነስ እንዲቻል ትኩረት እንደተሰጣቸውም ተናግረዋል፡፡

በዚህም በእነዚህ አካባቢዎች የመኸር ምርትን ጥራቱን በጠበቀ እና ከብክነት በጸዳ መልኩ ሰብልን መሰብሰብ እንዲቻል የተለያዩ ስራዎች እየተሰሩ ነው ብለዋል፡፡

በተጨማሪም የመስኖ ስራዎችን ማጠናከር ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰው፥ ከስንዴ ልማት በተጨማሪ የአትክልትና ፍራፍሬ ምርትን ለመጨመር በመደበኛ የመስኖ ስራ እየተከናወነ ይገኛልም ነው ያሉት፡፡

በመደበኛ መስኖ ከአትክልት፣ ፍራፍሬ እና ስራስር ምርቶች ጋር በተያያዘ 349 ሺህ ሄክታር መሬት የታረሰ ሲሆን፥ 311 ሺህ ሄክታር የሚሆነው መሬት በዘር መሸፈኑን ገልጸዋል፡፡

ይህም ከታረሰው 89 በመቶው መሬት በዘር የተሸፈነ መሆኑን አስረድተዋል።

በበጋ የመስኖ ስንዴ 400 ሺህ ሄክታር መሬት ለማልማት ታቅዷል ያሉት ሚኒስትር ዲኤታዋ ከዚህም 16 ሚሊየን ኩንታል ምርት ለማግኘት መታቀዱን ጠቁመዋል፡፡

በመስኖ ስንዴ ልማት 256 ሺህ ሄክታር መሬት ታርሶ ÷ 146 ሺህ ሄክታር መሬት ወይንም 64 በመቶውን በዘር ተሸፍኗል ብለዋል፡፡

የግብርናውን ዘርፍ ለማጠናከር የሰብል ምርትን ከብክነት በጸዳ መልኩ ለመሰብሰብ የሚያስችሉ ቴክኖሎጂዎችን መጠቀም እንደሚገባም አውስተዋል፡፡

ከሰብል ልማት በተጨማሪም የአረንጓዴ አሻራ ችግኞች ላይ እንዲሰራበት ትኩረት ተሰጥቶበታል ነው ያሉት ሚኒስትር ዲኤታዋ ፡፡

ከህልውና ዘመቻው ጎን ለጎን መካከለኛ እና ሰፋፊ የመስኖ ግንባታ ፕሮጀክቶች እየተከናወኑ ነው ብለዋል፡፡

በ2014 ዓ.ም ግንባታቸው እንዲካሄድ 17 የመስኖ ፕሮጀክቶች በእቅድ የተያዙ ሲሆን ÷ ለማስፈጸሚያነትም 9 ነጥብ 8 ቢሊየን ብር በጀት እንደተያዘላቸውም ነው የተገለጸው፡፡

አካባቢዎን ይጠብቁ!
ወደ ግንባር ይዝመቱ!
መከላከያን ይደግፉ!

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.