Fana: At a Speed of Life!

የምስራቅ ዕዝ የመከላካያ ሰራዊት ቀንን አከበረ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 7፣ 2012(ኤፍ.ቢ.ሲ) የምስራቅ ዕዝ ስምንተኛውን የመከላካያ ሰራዊት ቀንን በጽዳት ዘመቻ፣ በደም ልገሳና በፓናል ውይይት በሀረር ከተማ አከበረ።

በዚህ የፓናል ውይይት ላይ የተገኙት የምስራቅ ዕዝ ዋና አዘዥ ሜጀር ጀነራል ዘውዱ
በላይ፥ ሰራዊቱ የሚያጋጥሙትን ችግሮች በማለፍ በአገሪቱ ሰላም እንዲሰፍን በቁርጠኝነት እየተንቀሳቀሰ ይገኛል ብለዋል።

በተለይ በቀጠናው የሚያጋጥሙ የጸጥታ ችግሮችን ለመከላከል ህብረተሰቡን ባሳተፈ መልኩ በትግዕስትና ጥንቃቄ ችግሮቹን እየፈታ ይገኛል፥ ለዚህም ሰራዊቱ ወስጣዊ አንድነቱንና ዝግጁነቱን በማጠናከር ለህዝብ ያለውን ወገንተኝነት ዳግም በተግባር ያረጋግጣል ሲሉ ተናግረዋል።

በተለይም በህዝብ ላይ የሚቃጡ የአካልና የንብረት ጥቃቶችን ህግ መሰረት ባደረገ መልኩ የመከላከል ሃላፊነታችንን በቁርጠኝነት እንወጣለን ብለዋል።

ዘንድሮ ከሚካሄደው አገራዊ ምርጫ ጋር ተያይዞ የሚከሰቱ ችግሮችን የመቅረፍና የህብረተሰቡን ሰላም ለማረጋገጥ የሚከናወኑ ስራዎች ተጠናክረው ይቀጥላል ሲሉ አንስተዋል።

አያይዘውም በአካባቢ የሚገኙ የሐይማኖት አባቶችና የአገር ሽማግሌዎችም የእርቅና የማግባባት ስራን በማጠናከር በህዝቦች መካከል የነበረውን ማህበራዊ ትስስር በማጠናከር ሰላም እንዲሰፍን ማድረግ ይገባል ብለዋል።

“ሰራዊታችንን ለድል ያበቁት ህዝባዊ ባህርያቶችና ቁልፍ እሴቶቹ በተቋማዊ ለውጥ ትግበራ” በሚል ርዕስ በፓናል ውይይቱ ላይ ጽሁፍ ያቀረቡት በምስራቅ ዕዝ የ13ኛ ክፍለ ጦር ዋና አዛዥ አሊጋዝ ገብረ በበኩላቸው፥ የህግ የበላይነት እንዲከበርና ሰላም እንዲሰፍን ሰራዊቱ እየከፈለ የሚገኘውን መስዋዕትነት አጎልብቶ ይቀጥላል ብለዋል።

በአካባቢው የሚገኙ አመራርና የጸጥታ አካላት፣ የአገር ሽማግሌዎችና የሀይማኖት አባቶች የሚያጋጥሙ ችግሮችን በጋራ በመፍታት የተጀመረውን ለውጥ ማስቀጠል ይገባልም ሲሉ ተናግረዋል።

በፓናል ውይይቱ ላይ ከሐረሪ ክልል የተገኙት የማህበረሰብ ተወካይ በክልሉ ሰላም እንዲሰፍን ትዕግስት በተሞላበት መልኩ የሚያከናውነው ስራ ውጤት እያመጣ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

ይህንንም ስራ ለማጠናከር በአካባቢያቸው አልፎ አልፎ የሚከሰቱ ችግሮችን ሳይባባሱ በፍጥነት እልባት ለመስጠት የእርቅና ሽምግልና ኮሚቴ በማዋቀር የበኩላቸውን ስራ እያከናወኑ እንደሚገኙና ይህም ስራ በሌሎች አካዎችም በማስፋፋት ላይ እንደሚገኙ መናገራቸውን ከሀረሪ ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.