Fana: At a Speed of Life!

ህብረቱ የአስቸኳይ ጊዜ የአየር ንብረት ለውጥ ፈንድ ማቋቋም የሚያስችል ንድፈ ሃሳብ ለአባል ሀገራቱ አቀረበ

አዲስ አበባ ፣ የካቲት 7፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የአፍሪካ ህብረት የአስቸኳይ ጊዜ የአየር ንብረት ለውጥ ፈንድ ማቋቋም የሚያስችል ንድፈ ሀሳብ ለአባል ሀገራቱ አቀረበ።

አፍሪካ ለአየር ንብረት ለውጥ ያላት ተጋላጭነትና በለውጡ በሚከሰቱ አደጋዎች ከፍተኛ ተጎጂ እንደሆነች ይነገራል።

የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖው የአፍሪካን ዜጎች ኑሮ የማሻሻልና የኢኮኖሚ ልማት ስራዎች በሚፈለገው መልኩ እንዳይሄዱ እክል እየፈጠረ ይገኛል።

የአየር ንብረት ለውጥ ተመራማሪዎች በለውጡ የሚደርሱ አደጋዎችን የመቋቋምና የመከላከል አቅማቸው አነስተኛ እንደሆነና ለአቅም ማነሱ አብዛኛውን ድርሻ የሚይዘው የፋይናንስ እጥረት እንደሆነ ያነሳሉ።

የአፍሪካ ህብረት የገጠር ኢኮኖሚና ግብርና ኮሚሽነር ሚስ ጆሴፋ ሳኮ አፍሪካ የአየር ንብረት ለውጥ ለመቋቋም የሚያስችላት ፈንድ ለማቋቋም የኅብረቱ ንድፈ ሀሳብ ለአገራቱ መቅረቡን ገልጸዋል።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በፈረንጆቹ በ2015 “ኮፕ 21” በሚል ስያሜ በፈረንሳይ መዲና ፓሪስ ባካሄደው ስብስባ ሀገራት በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ከስምምነት መድረሳቸው ይታወቃል።

ከስምምነቱ አንዱ ያደጉ እስከ 2025 በየዓመቱ አፍሪካን ጨምሮ በማደግ ላይ ለሚገኙ ሀገራት በአየር ንብረት ለውጥ የሚደርስባቸውን አደጋዎች ለመቋቋምና ለመላመድ በየዓመቱ 100 ቢሊየን ዶላር ገንዘብ መስጠት ነው።

እንደ ጆሴፋ ሳኮ ገለጻ፤ ተግባራዊ በሆነው የፓሪስ የአየር ንብረት ለውጥ ስምምነት ቃል ከተገባው ገንዘብ የተገኘው ሃብት ውስንና ለሚደርሱት ችግሮችም ምላሽ የሚሰጥ አይደለም።

በአየር ንብረት ለውጡ እየተከሰቱ ያሉ አደጋዎች በአፍሪካ ያለውን የምግብ ደህንነት ለማረጋገጥ እየተከናወነ ባለው ስራ ላይ እክል እየፈጠረ መሆኑን መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

በአፍሪካ ሰብዓዊ ጉዳዮችን በተመለከተ ተግባራዊ እየሆኑ ያሉ ልዩ ፈንዶች መኖራቸውንና አህጉሪቷ አሁን እየገጠማት ያለውን የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖ ለመቋቋም የአስቸኳይ ጊዜ የአየር ንብረት ለውጥ ፈንድ ማቋቋም በጣም አስፈላጊ ጉዳይ እንደሆነም አመልክተዋል።

የአፍሪካ ሀገራት የአየር ንብረት ለውጥን መቋቋም ለሚያስችሉ ስራዎች ከዓመታዊ በጀታቸው ሁለት በመቶ የሚሆነውን እያዋሉ እንደሚገኙ ጠቁመው፤ ይህም በዘላቂነት መጠናከር እንዳለበት አሳስበዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.