Fana: At a Speed of Life!

በአሸባሪው ህወሓት የወደመው የሐይቅ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ሥራ ጀመረ

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 11፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በአሸባሪው ህወሓት የወደመው የሐይቅ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል የኤካ ኮተቤ አጠቃላይ ሆስፒታል ባደረገው ድጋፍ ሥራ ጀምሯል፡፡
የሐይቅ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታልን ሥራ ለማስጀመር ኃላፊነት የተረከበው የኤካ ኮተቤ አጠቃላይ ሆስፒታል 7 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር የሚገመት የሕክምና መሣሪያዎችን እና መድኃኒቶችን ባለፉት አምስት ቀናት ሲያስገባ ቆይቷል።
አሚኮ ከቦታው ተገኝቶ እንዳረጋገጠው÷ ዛሬ ድጋፍ በተደረገው የሕክምና ቁሳቁስ እና መድኃኒቶች ተገልጋዮች አገልግሎት አግኝተዋል፡፡
የኤካ ኮተቤ አጠቃላይ ሆስፒታል በአሸባሪው እና ወራሪው ቡድን ውድመት እና ዝርፊያ ለደረሰበት የሐይቅ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል 7 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር የሚገመት የሕክምና መሣሪያዎች እና መድኃኒት ድጋፍ አድርጓል።
የአገልግሎቱ ተጠቃሚዎች በበኩላቸው÷ ባለፉት ወራት የሽብር ቡድኑ በፈጠረው ወረራ እና ውድመት መታከም አለመቻላቸውን አስረድተው÷ ሆስፒታሉ አገልግሎት በመስጠቱ መደሰታቸውን ገልጸዋል።
ከታካሚዎቹ አንዳንዶች የሽብር ቡድኑ በንጹሃን ላይ በሰነዘረው ጥቃት ተጎጅ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
የኤካ ኮተቤ አጠቃላይ ሆስፒታል ሥራ አስኪያጅ ዶክተር ያሬድ አግደው÷ የሐይቅ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታልን ለማደራጀት የሚያስፈልጉ የሕክምና ቁሳቁስ በአምስት ቀናት ውስጥ ማስገባት መቻላቸውን ጠቁመው÷ ወደ ሆስፒታሉ የገባው ድጋፍም 7 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር የሚገመት መሆኑን አረጋግጠዋል።
የሕክምና ቁሳቁሱም የድንገተኛ፣ የወሊድ፣ የላቦራቶሪ የፋርማሲ፣ የተኝቶ ሕክምና እና የቀዶ ጥገና አገልግሎት ለመስጠት የሚያግዙ መሆናቸው ተገልጿል፡፡
ከሕክምና ማሳሪያዎች ጋር መድኃኒቶችም ቀርበዋል ብለዋል።
የኤካ ኮተቤ የተለያዩ የሕክምና ባለሙያዎችም ከነገ ጀምረው ወደ ሆስፒታሉ ገብተው አገልግሎት እንደሚሰጡ ተናግረዋል።
የሐይቅ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ሥራ አስኪያጅ አራጋው ደምሴ÷ ሆስፒታሉ በዘራፊ እና ወራሪ ቡድኑ በመውደሙ ከግማሽ ሚሊየን በላይ ለሚሆኑ የህብረተሰብ ክፍል የሕክምና አገልግሎት ሲሰጥ የቆየ ሆስፒታል ለወራት አገልግሎቱ ተቋርጦ መቆየቱን ተናግረዋል።
በዚህም የበርካታ ሰዎች ሕይወት አልፏል፤ ብዙዎችም በሕመም እንዲሰቃዩ ተደርገዋል ነው ያሉት።
አካባቢዎን ይጠብቁ!
ወደ ግንባር ይዝመቱ!
መከላከያን ይደግፉ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.