Fana: At a Speed of Life!

ሕወሓት በውጊያ ከሞቱና ከቆሰሉ ታጣቂዎቹ የተወሰኑትን ይዞ በመሸሽ በ“መንግሥት የተፈጸመ ጅምላ ጭፍጨፋ ነው” ለሚል የሀሰት ፕሮፖጋንዳ እየተዘጋጀ ነው

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 12፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ ጥምር ጦር የተቀናጀ ጥቃት ሽንፈት ተከናንቦ ወደ ትግራይ የሸሸው ወራሪው የህወሓት ኃይል በየአውደ ውጊያው ከሞቱና ከቆሰሉ ታጣቂዎቹ የተወሰኑትን ወደ ትግራይ ይዞ በመሸሽ ላይ መሆኑን ታማኝ የመረጃ ምንጮቻችን ተናግረዋል፡፡
ቡድኑ ወቅታዊ ሁኔታን አስመልክቶ በምስጢር ባደረገው ስብሰባ የኢትዮጵያ ጥምር ጦር አሁን ባለው ቁመናና ግስጋሴ ወደ መቀሌ በአጭር ጊዜ ሊገባ ይችላል የሚለውን መላምት ሊያጋጥሙት ከሚችሉት ችግሮች እንደ አንዱ አድርጎ የገመገመ ሲሆን፥ ይህ ከተከሰተ በሚልም ዓለም አቀፉን ማህበረሠብና የትግራይን ህዝብ የሚያጭበረብርበት የሴራ እቅድ ማዘጋጀቱ ታውቋል፡፡
እንደ መረጃ ምንጮቻችን፤ ወራሪው የህወሓት ኃይል ባዘጋጀው እቅድ መሰረት በየአውደ ውጊያው ከሞቱና ከቆሰሉ ታጣቂዎቹ የተወሰኑትን ወደ ትግራይ ይዞ በመሸሽ የመከላከያ ሠራዊት ወደ ትግራይ ከገባ “የመንግሥት ኃይል ጅምላ ጭፍጨፋ ወይም የዘር ማጥፋት እየፈጸመ ነው” በማለት በሙትና ቁስለኛ ታጣቂዎቹ ምስል ለመነገድ አስቧል፡፡
እየተቀነባበረ ያለው ሴራ ሰሞኑን የተመድ ሰብአዊ መብቶች ምክር ቤት ልዩ ስብሰባ አድርጎ ካሳለፈው ውሳኔ ጋር ተመጋጋቢ መሆኑን የጠቆሙት ምንጮቻችን፥ ምክር ቤቱ ከዚህ ቀደም ከኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ጋር በመሆን ምርመራ አድርጎ ሪፖርት የቀረበበትን ጉዳይ እንደ አዲስ እንዲታይ በምዕራባውያን ዘዋሪነት ያሳለፈው ውሳኔ ለዚህ ሴራ አጋዥ እንዲሆን ታቅዷል የሚል ጥርጣሬ ማሳደሩን ገልጸውልናል፡፡
የመከላከያ ሠራዊት ወደ ትግራይ ቢገባ ቡድኑ ከየግንባሩ የሰበሰባቸውን ሙትና ቁስለኛ ታጣቂዎቹን ምስል በማሰራጨት የተመድ ሰብአዊ መብቶች ምክር ቤት የሰሞኑ ውሳኔ ምክንያታዊ ነው የሚል ተቀባይነት እንዲያገኝ ለምእራባውያን ታዛዥ ከሆኑ የተለያዩ ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ድርጅቶችና መገናኛ ብዙሃን ጋር ተናቦ ለመስራት የታቀደ መሆኑን የገለጹት ምንጮቻችን፥ የተመድ ውሳኔ የሀገር ሉዓላዊነት የሚጋፋና ፖለቲካዊ አንድምታ ያለው ነው በሚል ከ22 ሀገራት ተቃውሞ እንደገጠመው አስታውሰዋል፡፡
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.