Fana: At a Speed of Life!

17 ጁንታ ደምስሰው የተሰውት የእነብሴ ሳር ምድሩ ጀግና

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 12፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) 17 የህወሓት ሽብር ቡድን ታጣቂዎችን ደምስሰው እየፎከሩ የተሰውት የእነብሴ ሳር ምድሩ ጀግና ለበርካታቶች አርአያ የሚሆን ጀብዱ ፈጽመዋል፡፡
 
አቶ ደስታ መኮንን ይባላሉ ነዋሪነታቸው ደግሞ በምስራቅ ጎጃም ዞን እነብሴሳር ምድር ወረዳ ነው፡፡
 
የ51 ዓመቱ ጎልማሳ አቶ ደስታ ከ1980ዎቹ ጀምረው ለሀገራቸው አንድነትና ሉዓላዊነት ስለእውነትና ስለፍትህ ሲታገሉ ቆይተዋል፡፡
 
አሁንም አሸባሪው ህወሓት በሀገሪቱ ላይ ጦርነት ከከፈተበት ጊዜ ጀምሮ ለሶስት ጊዜ በተለያዩ ግንባሮች በመሰለፍ ከጠላት ጋር ተፋልመው ወደ አካባቢያቸው በመመለስ ደግሞ ሚሊሻዎችን ያሰለጥኑ ነበር።
 
ያለባቸው የልብ ህመም እና ጨጓራ በሽታ እያሰቃያቸው መድኃኒት ይወስዱ የነበሩት አቶ ደስታ፥ አሸባሪ ቡድኑ በሀገሬ ላይ ጦርነት ከፍቶ ንፁሃንን እየገደለ ፣ ሴቶችን እየደፈረ እና ሃብትና ንብረትን በእብሪት እያወደመ እዚህ አልቀመጥም በማለት ለ4ኛ ጊዜ ዘምተዋል፡፡
 
በዚህ ወቅትም በቤተሰቦቻቸው እና ጓደኞቻቸው ያለባቸውን ችግር ግምት ውስጥ በማስገባት ሃሳባቸውን እንዲቀይሩ ጠይቀዋቸው ነበር፡፡
 
በአሸባሪ ቡድኑ አረመኔያዊ ድርጊት ክፉኛ የተቆጡት አቶ ደስታ የቀረበላቸውን ጥያቄ ውድቅ በማድረግ በተለያየ ጊዜ ያሰለጠኑትን ሚሊሻ እየመሩ ወደ ወሎ ግንባር መዝመታቸውን ቤተሰቦቻቸው ይናገራሉ።
 
በወሎ ግንባር አብሯቸው ተሰልፎ የነበረው ወንድማቸው አቶ መልካም አቶ ደስታን በአውደ ውጊያ ላይ የፈጸሙትን ጀብድ እንዲህ ሲል ያስታውሳል፡፡
 
“ወንድሜ 17ቱን የጠላት ጦር አባላት ሲገድል እየፎከረ ለሚመራው ሰራዊትም ሽፋን በመስጠት የጠላትን መሳሪያ ጭምር እየማረከ” ነበር ብሏል፡፡
 
“ወንድሜ 8 ልጆቹንና ደካማ እናታችንን ትቶ ከራሱና ከቤተሰቡ በላይ ሀገሬን ብሎ ዘምቶ መስዋዕት በመሆኑ ለቤተሰቦቹ ብዙ ቢያጎልብንም በፈጸመው ጀብድ ግን ተፅናንተናል” ነው ያለው።
 
ባለቤታቸው ወይዘሮ ውድ አላት ያለውና ልጆቻቸው ወጣት ባዩ ደስታ እና ዘላለም ደስታም ÷ “አባታችን ሙሉ ጊዜውን ከቤተሰቦቹ በላይ ለህዝብና ለሀገር ሰጥቶ በጀግንነት መሰዋቱ ኢትዮጵያ እንደ ሀገር እንድትቀጥል ካለው ጽኑ እምነት የመነጨ ነው” ይላሉ፡፡
 
“ያለበት የጤና ችግር እና የቤተሰቡ ሁኔታ ሳያግደው ሀገሬን እዳለ ነው አባታችን ለሀገርና ህዝብ ሲል የተሰዋው” ብለዋል ቤተሰቦቹ ።
 
“ዛሬ አባታችንን በማጣታችን ልባችን ቢሰበርም ነገ ሀገራችን ነፃ ወጥታ ህዝባችን ደስተኛ ሲሆን ስናይ ግን የኛን አባት በመሰሉ ጀግኖች የህይወት መስዋዕትነት የተገኘ መሆኑን ስለምናውቅ እንፅናናለን” ይላሉ።
 
አቶ ደስታ መኮንን ለሀገራቸው አንድነት እና ሉዓላዊነት ሰሉ በጀግንነት እስከተሰውበት ጊዜ ድረስ የእነብሴ ሳር ምድር ወረዳ ሚሊሻ ጽህፈት ቤት የሰው ኃይል ስምሪት ባለሙያ በመሆን አገልግለዋል።
 
በአበበ የሸዋልኡል
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.