Fana: At a Speed of Life!

የአፍሪካ ባህላዊ መሪዎች መድረክ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው

አዲስ አበባ፣ የካቲት 7፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የአፍሪካ ባህላዊ መሪዎች መድረክ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።

መድረኩ በዋናነት “የአፍሪካ ባህላዊ መሪዎች ጉባኤ” እንዲመሰረት የማድረግን አላማ የሰነቀ መሆኑ ተገልጿል።

በተጨማሪም የአፍሪካ ትልቅ ችግር የሆነው የሰላምና ጸጥታ ጉዳይ ላይ የመፍትሄ ሀሳቦችን ለመጠቆምና ሰላም ለማምጣት በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ ለመምከርም እንደሆነ ተጠቁሟል።

የሀገር በቀል ዕውቀቶች ጥናትና ምርምር ባለሙያና የመድረኩ አስተባባሪ አቶ አብዱልፈታህ አብደላ እንደገለጹት፥የባህላዊ አስተዳደር መሪዎቹ ለአፍሪካ አህጉር ፈተና በሆኑ ጉዳዮች ላይ መክረው የመፍትሄ ሃሳብ ያመነጫሉ።

ከአፍሪካ ውጪ ያሉ የዳያስፖራ ማህበረሰብ አባላትም ወደ አህጉሪቱ መጥተው ልማትና ኢንቨስትመንት እንዲስፋፋ በማድረግ ተሳትፏቸውን እንዲያጎለብቱ የሚቻልበት ሁኔታ ላይ የባህላዊ አስተዳደር መሪዎቹ ይመክራሉ።

ለአፍሪካ መጥፎ ገጽታ የሆነውን ስደት እንዲቆምና ሁለንተናዊ እድገት እንዲመዘገብ ለማድረግ የሚያስችሉ ጉዳዮች ዙሪያ የሚመክሩ መሆኑን አቶ አብዱልፈታህ ጠቁመዋል።

ኢትዮጵያ የአፍሪካ ህብረት መቀመጫ በመሆኗ እና በየአመቱም ከምታስተናግደው የመሪዎች ጉባኤ ጎን ለጎን የባሕላዊ መሪዎቹን ጉባኤም እንድታስተናግድ ለማድረግ እንደታሰበም ተናግረዋል።

ይህም መድረክ ሁሉም የአፍሪካ የባህል መሪዎች የሚተዋወቁበትና አብረው በጋራ ልማታዊ እንቅስቃሴዎችን የሚያመቻቹበት ሁኔታ ለመፍጠር እንደሚረዳ አመልክተዋል።

ዛሬ አዲስ አበባ ውስጥ በተካሔደው መድረክ የኮትዲቫር፣ የካሜሮንና የዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ የባህል መሪዎችን ጨምሮ ሌሎችም እንግዶች መታደማቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

የባህል መሪዎቹ በኢትዮጵያ በሚኖራቸው ቆይታ ከተለያዩ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች ጋር ይነጋገራሉ ተብሎ ይጠበቃል።

መድረኩ ለሁለት ቀናት የሚቆይ ሲሆን በነገው መርሀ-ግብርም በቀጣይ አምስት አመት እቅድ ላይ ውይይት የሚደረግ መሆኑ ተገልጿል።

“የአፍሪካ ባህላዊ መሪዎች ጉባኤ” ለማቋቋም የሚያስችለው ዋና ስብሰባ ከሶስት ወራት በኋላ ስለሚደረግ ከሁሉም የአፍሪካ አገሮች የሚመጡ ባሕላዊ መሪዎች ይሳተፋሉ ተብሎ ይጠበቃል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.