ቴክ

ኢራን የባለስቲክና የክሩዝ ሚሳኤሎችን አስወነጨፈች

By ዮሐንስ ደርበው

December 22, 2021

 

አዲስ አበባ፣ታህሳስ 13፣2014(ኤፍ ቢሲ) ኢራን የባለስቲክ እና የክሩዝ ሚሳኤሎችን በትናንትናው እለት ማስወንጨፏን አስታውቃለች።

የኢራን አብዮታዊ ዘብ እንዳስታወቀው በባህረ ሰላጤው አካባቢ በተደረገ ወታደራዊ ልምምድ ላይ የባሊስቲክ እና ክሩዝ ሚሳኤሎችን አስወንጭፋለች።

የኢራን አብዮታዊ ዘብ ዋና አዛዥ ጀኔራል ሁሴን ሳላሚ፥ የተወነጨፉት የባሊስቲክ ሚሳኤሎች 2 ሺህ ኪሎ ሜትር መጓዝ የሚችሉ ሲሆን፥ የሃገሪቱ ባላንጣ ሃገራት ወደሚባሉት እስራኤል እና የአሜሪካ ጦር ሰፈሮች የመድረስ አቅም አላቸው ነው ያሉት።

የአምስት ቀናት የጦር ልምምዱ ባለፈው ሰኞ የተጀመረ ሲሆን፥ አምስት የክሩዝ ሚሳኤሎችን በአንድ ጊዜ ማስወንጨፍንና እና እያንዳንዳቸው ሁለት ኢላማዎችን መምታት የሚችሉ የታጠቁ ሰው አልባ አውሮፕላኖችን ማብረርን ያካተተ እንደነበር ሚድል ኢስት ሞኒተር ዘግቧል።