Fana: At a Speed of Life!

ሕዝብን ከረሃብ እልቂት የታደገው የብጹዕ አቡነ ኤርሚያስ አዋጅ በወልድያ ከተማ

አዲስ አበባ ፣ ታህሳስ 13 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) አሸባሪው ቡድን ወልድያ ከተማን በመውረር ከባድ ዘረፋ እና ውድመት አድርሷል፡፡

በእነዚህ የወረራ እና ዝርፊያ ቀናቶች ውስጥ ደግሞ የሃይማኖት አባቶች ሕዝብን በማጽናናት ከወራሪው ቡድን ፊት ለፊ በመጋፈጥ ያደረጉት አባታዊ ተጋድሎ ታሪክ የሚዘክረው ነው፡፡

ደግ አባት በክፉ ቀን መጠጊያ ነው እንደሚባለው የሰሜን እና የደቡብ ወሎ እንዲሁም የኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል ብጹዕ አቡነ ኤርሚያስም ይህንኑ በተግባር አሳይተዋል ይላሉ የወልድያ ከተማ ነዋሪዎች፡፡

አሸባሪዎቹ ወደ ከተማው ገብተው ሕዝብን ሲያሸብሩ ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ኤርሚያስ ዝም ብለው አልተቀመጡም ከመንበረ ጸባዎታቸው ዝቅ ብለው ወደ ሕዝብ መንደሮች ገቡ የሚያሸብሩትን በአባታዊ ግሳጼ በመገሰጽ የሚያደርጉትን ተቃወሙ፡፡

ሕዝቡም የሚያጽናናው እና ከጎኑ ሆኖ የሚመራው እንዳለ በማወቁ የተረበሸው ከተማ መጠነኛ መረጋጋት ታየበት፤ አሸባሪዎቹ ግን ማሸበራቸውን ቀጥለዋል ሕዝቡም ከአባቱ የሚሰጠውን ምክር እየተቀበለ አሸባሪዎቹን በትእግስት ያልፍ ነበር፡፡

አሸባሪ ቡድኑ የሚፈጽመው ሰቆቃ ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ኤርሚያስ ባይኖሩ የሕዝቡ ስቃይ ይበረታ ነበር ይላሉ የከተማዋ ነዋሪዎች፡፡

ሃይማኖት ሳይለዩ ያለው ለሌለው እንዲያካፍል በማድረግ ሕዝቡን ከርሃብና ከእልቂት በመታደግ ትውልድ ሁሉ የማይረሳው ተግባር መፈጸማቸውን አሚኮ ያነጋገራቸው የወልድያ ከተማ ነዋሪዎች ተናግረዋል፡፡

የወልድያ ከተማ ነዋሪው አቶ ሞላ እጅጉ ስለ ብጹዕ አቡነ ኤርሚያስ ምስክርነት ሲሰጡ “በደስታ እና በሀዘን ጊዜ ከእኛ ያልተለዩ፤ ሕዝቡን ከተኩላዎች ያተረፉ የዚህ ትውልድ ጀግና አባት” ሲሉ ገልጸዋቸዋል፡፡

ሌላኛዋ የወልድያ ከተማ ነዋሪ ወይዘሮ ሜላት ደምሴ ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ኤርሚያስ በክፉ ቀን ከጎናችን ሆነው ከሞት፣ ከስደት እና ከርሃብ ታድገውናል እና ትውልድ ሁሉ ሲያመሰግናቸው ይኖራል ብለዋል፡፡

እሳቸው ባይኖሩ የብዙ ሰዎች ሕይወት ያልፍ እንደነበር ነው ነዋሪዎቹ የነገሩን፡፡

ይህንን መልካም ሥራ ለሠሩት ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ኤርሚያስ ረጅም ዕድሜና ጤና ተመኝተውላቸዋል፡፡

የሰሜን እና የደቡብ ወሎ እንዲሁም የኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል ብጹዕ አቡነ ኤርሚያስ በባለፉት አምስት ወራት ውስጥ ብዙ አሳዛኝ ክስተቶችን መመልከታቸውን ገልጸዋል፡፡

በተለይም ወልድያ ከተማ በሽብር ቡድኑ በተያዘችበት ወቅት ሕዝቡ ምግብ፣ መድኃኒት፣ መብራት፣ ከሰል፣ እንጨት እና የመሳሰሉትን በማጣት ያሳለፈው የችግር ቀን ከሕሊናቸው የማይጠፋ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በአንድ ጊዜ ሁሉም ነገር የተቋረጠበትን ሕዝብ ማየት እንደሃይማኖት አባት ከባድ ነው ያሉት ብጹዕ አቡነ ኤርሚያስ፥ በነበረው ችግር ለኢትዮጵያ ብዙ ዋጋ የከፈሉ አባቶች እና እናቶች ሲራቡ አይተዋል፣ በምግብ እጦት ሲያለቅሱ የነበሩ ሕፃናትን ተመልክተዋል፤ በሕክምና እጦት ሕይወታቸው ያለፉ እናቶችን ቀብረዋል፤ እጅግም አዝነዋል፡፡

ከቤታቸው የወለዱ እናቶችም “መውለድስ በሰላም ወልጀአለሁ፤ ከቤቴ ግን ምንም የሚቀመስ የእህል ዘር የለም፤ የሚቻለውን ሁሉ ያድርጉልን” የሚል ደብዳቤም ከወላድ እናቶች ደርሷቸዋል፤ እጅግ የደከሙ ሽማግሌዎችን ባገኙበት ወቅትም ርሃባቸውን ስሜት ለመግለጽ “አባ ፊቴን እዩኝ እማ” የሚሉም ገጥሟቸዋል፡፡

ይህን ሁሉ ችግር በሌለ ነገር ለመፍታት ቢቸገሩም የሕዝቡን ብሶት እና እሮሮ በመስማት በቸልታ አላለፉትም፤
የሕዝብ ስቃይ፣ ርሃብ፣ እንግልት እና ሞትን ለመታደግ አደባባይ ወጡ፤ ከሕዝቤ በፊት ራሴ መስዋእት ሁኜ ሕዝቤን አድነዋለሁ ብለው አደባባይ በመውጣትም ሁላችሁም ያላችሁን አምጡ አብረን ቀምሰን አብረን እንሙት የሚል አዋጅ አወጁ፡፡

ነዋሪዎቹም የወራሪው ቡድን እንዳይዘርፋቸው ደብቀው ያኖሩትን ገንዘብ ሁሉ እንደሰጧቸው ብጹዕ አቡነ ኤርሚያስ ነግረውናል፡፡

በአጭር ቀናት ውስጥም 5 ነጥብ 9 ሚሊዬን ብር መሰብሰብ ችለዋል፡፡

የተሰበሰበውን ገንዘብም ጊዜ ሳያባክኑ በእምነት ሳይለዩ ለችግረኞች ሁሉ በማካፈል ከአዋሳኝ አካባቢዎች በጋማ ከብቶች እህል እና መድኃኒት ተገዝቶ እንዲገባ አድርገዋል፡፡

ብጹዕ አቡነ ኤርሚያስ ተገዝቶ የገባው እና በየቤቱ የነበረውን እህል እንዲያስፈጩ የእህል ወፍጮ ማስጀመር ስለነበረባቸው 14 የእህል ወፍጮ ባለቤቶች እንዲከፍቱ አድርገዋል፡፡ ለእነዚህ ወፍጮ ባለቤቶችም ከወራሪው ቡድን እየተደበቁ ነዳጅ እንዲጠቀሙ በማድረግ ያን ክፉ ቀን አልፈዋል፡፡

በዚህም ሥራ የብዙዎችን ነፍስ ታድገዋል፤ ይህ ባይሆን በአካውንታቸው ብዙ ገንዘብ እያላቸው በርካቶች ለሕልፈት ይዳረጉ ነበር ያሉት ብጹዕ አቡነ ኤርሚያስ ሕዝቡ ክፉ ጊዜ ማሳለፉን አስታውሰዋል፡፡

በዚህ ሁሉ ውጣውረድ ውስጥ የኢትዮጵያዊያን የመረዳዳት ባሕል እንዳልጠፋ ማረጋገጣቸውን ብጹዕ አቡነ ኤርሚያስ አስረድተዋል፡፡

ሕዝቡ ያለውን ተካፍሎ እነዚያ የጨለማ ወራቶችን ሲያሳልፍ መመልከታቸውንም ተናግረዋል፡፡

በዚህም ኢትዮጵያዊያን ሩህሩህ ሕዝቦች መሆናቸውን በመመልከታቸው እንደ ሃይማኖት መሪ ደስተኛ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያዊያን የመተሳሰብ፣ የመተዛዘን እና ችግርን በጋራ የማለፍ ጥበብ ለዘመናት ጸንቶ መቀጠል ያለበት መልካም ባሕሪ ነው ብለዋል ብጹዕ አቡነ ኤርሚያስ፡፡

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የሰሜን ወሎ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ አባ ኀይለ ገብርኤል ፍሰሃ መኮንንም ብጹዕ አቡነ ኤርሚያስ ሕዝቡን ለመታደግ የሚያስችሉ ሥራዎችን እንደሠሩ መስክረዋል፡፡

አሸባሪው ቡድን ወደ ትልልቅ ተቋማት በመግባት የሚዘርፈውን ዘርፎ የሚያወድመውን አውድሞ ከወጣ በኋላ የቀረውን ሀብት በመሰብሰብ ሥራ እንዲጀምር ማድረጋቸውን የገለጹት አባ ኀይለ ገብርኤል ፍሰሃ ወደ ሆስፒታሉ 32 የሕክምና ባለሙያዎችን ከየቤታቸው በማሰባሰብ ሥራ አስጀምረዋል፤ እነዚያ ባለሙያዎችም ከ22 ሺህ በላይ ሕሙማን አገልግሎት እንዲያገኙ አድርገዋል፤ መድኃኒት በአህያ ተጭኖ ከሌላ አካባቢ እንዲገባ ሲያደርጉ እንደቆዩም ተናግረዋል፡፡

ብጹዕ አቡነ ኤርሚያስ በከተማዋ እና አካባቢው የሚገኙ ሕዝቦችን እየተዘዋወሩ አረጋግተዋል፤ ያለው ለሌለው አካፍሎ እንዲመገብ አድርገዋል ነው ያሉት፡፡

ሀጂ ያሲን እንድሪስ “ብጹዕ አቡነ ኤርሚያስ የወልድያን ሕዝብ ከሌሎች አባቶች ጋር በመሆን የታደጉ ናቸው ብለዋል፡፡

ሀጂ ያሲን እንዳሉት የወራሪው ቡድን የሰውልጅ የማያደርገውን ድርጊት ሁሉ በሰዎች፣ በእምነት ተቋማት፣ በመንግሥት እና በግል ተቋማት ፈጽሟል፡፡

በእነዚህ ሁሉ ሂደቶች ግን የሃይማኖት አባቶች ከሕዝብ ጎን በመቆም ሕዝቡ የረሃብ እና ሌላም ችግር እንዳይደርስበት ማድረጋቸውን ነው የገለጹት፡፡

በሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ኤርሚያስ አስተባባሪነት ከሕዝበ ሙስሊሙ ብዙ ሚሊዮን ብር በመሰብሰብም ለወገን በብድር መልክ እንዲሰጥ ማድረጋቸውን ተናግረዋል፡፡

ሕዝቡን ከችግር ለማዳን ከሽብር ቡድኑ ፊት ለፊት ተጋፍጠናል ያሉት ሀጂ ያሲን ዛሬ ላይ ከዚህ ቀን በመድርሳቸውም ለፈጣሪ ምስጋና አቅርበዋል፡፡

አካባቢዎን ይጠብቁ!

ወደ ግንባር ይዝመቱ!

መከላከያን ይደግፉ!

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.