Fana: At a Speed of Life!

በሐረሪ ክልል በ11 ትምህርት ቤቶች አዲሱ የትምህርት ካሪኩለም የሙከራ ትግበራ ተጀመረ

አዲስ አበባ፣ታህሳስ 13፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በሐረሪ ክልል በሚገኙ 11 ትምህርት ቤቶች አዲሱ ካሪኩለም የሙከራ ትግበራ መጀመሩን የክልሉ ትምህርት ቢሮ አስታውቋል።
የክልሉ ትምህርት ቢሮ ሀላፊ አቶ ሙኽታር ሳሊህ እንደተናገሩት አዲሱ ካሪኩለም የሙከራ ትግበራ ለማስጀመር ሰፊ ርብርብ ሲደረግ ቆይቷል።
በአሁኑ ወቅትም በክልሉ በሚገኙ 10 አንደኛ ደረጃ እና አንድ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች አዲሱ ካሪኩለም የሙከራ ትግበራ ተጀምሯል ብለዋል።
በክልሉ በተለይም በአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች በተጀመረው የሙከራ ትግበራ በሐረሪ ፣ በአፋን ኦሮሞና አማርኛ የመማሪያ ቋንቋዎችትምህርት መሰጠት መጀመሩን ጠቁመው ለዚህም ባለሙያዎችና አስፈላጊ ግብአቶች መሟላታቸውን አብራርተዋል።
አዲሱ ካሪኩለም ከቀደሞው በተለየ መልኩ ሀገር በቀል እና የወቅቱ ቴክኖሎጂ እውቀቶችን ባካተተ መልኩ ክለሳ ተደርጎበት ወደ ስራ መገባቱንም አመላክተዋል።
በተጀመረው የሙከራ ትግበራ ሂደት የሚታዩ ክፍተቶችን በመለየትና በመቅረፍ በሚቀጥለው የትምህርት ዘመን በክልሉ በሚገኙ ሁሉም ትምህርት ቤቶች ሙሉ ትግበራ እንደሚጀመርም ጠቁመዋል።
ለ28 አመታት ሲተገበር በቆየው ካሪኩለም ሀገር በቀል እውቀቶችን እና የ21ኛው ክፍለ ዘመን እውቀቶችን ያካተተ ካለመሆኑም በተጨማሪ የተግባር ትምህርት ትኩረት እንዳልተሰጠውና በየክፍል ደረጃዎች ድግግሞሽ እንደሚስተዋል አንስተዋል።
በመሆኑም አዲሱን ካሪኩለም በቀጣይ አመት ሙሉ ለሙሉ ለመተግበር እየተከናወኑ ባሉ ተግባራት በተለይም የትምህርት አመራሩ እና የተማሪ ወላጆች የተዘጋጁ መፅሐፍቶችን በመገምገም እና ሌሎች ድጋፎችን በማድረግ ሚናቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።
በአሁኑ ወቅት በሀገር አቀፍ ደረጃ አዲሱ ካሪኩለም የሙከራ ትግበራ የጀመሩት ሐረሪ ክልልን ጨምሮ አምስት ክልሎች መሆናቸውን ከሐረሪ ኮሙኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
አካባቢዎን ይጠብቁ!
ወደ ግንባር ይዝመቱ!
መከላከያን ይደግፉ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.