Fana: At a Speed of Life!

ደሴና ኮምቦልቻን ጨምሮ በ30 ከተሞች የውሃ ተቋማት አገልግሎት መስጠት ጀመሩ

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 13፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በአማራ ክልል በ30 ከተሞች ውስጥ በአሸባሪው ህወሓት የወደሙ የውሃ ተቋማትን መልሶ በመጠገን ከ2 ነጥብ 5 ሚሊየን የሚበልጥ ህዝብ የንፁህ መጠጥ ውሃ ተጠቃሚ ማድረጉን የክልሉ ውሃና ኢነርጂ ቢሮ አስታወቀ።

በክልሉ የወደሙ የንፁህ መጠጥ ውሃ ተቋማትን ሙሉ በሙሉ አገልግሎት ለማስጀመር 1 ቢሊየን ብር እንደሚያስፈልግ ተገልጿል።

አሸባሪ ቡድኑ በወረራ ይዟቸው በነበሩ 82 ከተሞች ከ250 በሚበልጡ የንፁህ መጠጥ ውሃ ተቋማት ላይ ዘረፋና ውድመት ማድረሱን የቢሮው የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ አደም ወርቁ ተናግረዋል፡፡
በተቋማቱ ከ4 ሚሊየን በላይ ሕዝብ ይገለገል እንደነበር ያስታወሱት ሃላፊው፥ የአሸባሪ ቡድኑ ወራሪ ሀይል የቧንቧና የኤሌክትሮ መካኒካል መለዋወጫዎችን፣ ፓምፖችና ጄኔሬተሮች እንዲሁም የውሃ ጥራት መፈተሻ መሳሪያዎችን ዘርፎ የተቀሩትን ማውደሙን ገልጸዋል።

አሸባሪ ቡድኑ በኮምቦልቻ ከተማ የሚገኘውን የክልሉን ብቸኛ ተንቀሳቃሽ የውሃ ጥገና አገልግሎት ወርክ ሾፕ ጭምር ማውደሙን አቶ አደም ጠቅሰዋል።

የአራት ዞን የውሃ መምሪያዎችን ጨምሮ የ76 ወረዳዎችንና ከተማ አስተዳደሮችን ውሃና ኢነርጂ መምሪያ ጽህፈት ቤቶችን መዝረፉንና ማውደሙንም ተናግረዋል።

ከአሸባሪው ቡድን ነፃ በወጡ አካባቢዎች እስካሁን 53 የንፁህ መጠጥ ውሃ ተቋማት ተጠግነው አገልግሎት መስጠት መጀመራቸውን ጠቁመው÷ ለጥገናው 116 ሚሊየን ብር ወጪ መደረጉን አመላክተዋል።

ቢሮው በሌሎች ከተሞች የወደሙና የተዘረፉ የውሃ ተቋማትን ሥራ ለማስጀመር በአራት ቀጠናዎች የባለሙያዎች ቡድን እያሰማራ መሆኑን ኢዜአ ዘግቧል።

 

አካባቢዎን ይጠብቁ!
ወደ ግንባር ይዝመቱ!
መከላከያን ይደግፉ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.