Fana: At a Speed of Life!

“ዘመቻ ለኅብረ ብሔራዊ አንድነት” የመጀመሪያውን ግብ በማሳካት ተልዕኮውን ማጠናቀቁን የመንግስት ኮሚኒኬሽን አገልግሎት ገለፀ

አዲስ አበባ ፣ ታህሳስ 14 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የተመራው “ዘመቻ ለኅብረ ብሔራዊ አንድነት”  በአሸባሪው ሃይል የተወረሩ አካባቢዎችን በማስለቀቅ የመጀመሪያውን ግብ በማሳካት ተልዕኮውን ማጠናቀቁን የመንግስት ኮሚኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዶክተር ለገሰ ቱሉ ገለጹ።

ሚኒስትሩ ዛሬ በሰጡት መግለጫ ዘመቻው ቡድኑን ከወረራቸው አካባቢዎች ጠራርጎ የማስወጣትና ዳግም ለኢትዮጵያ ስጋት የማይሆንበትን ደረጃ ላይ ማድረስ ያለመ እንደነበር አስረድተዋል።

በዚህ መሰረት ወራሪው ቡድን ከአፋር ክልል ሙሉ በሙሉ እንዲሁም ከአማራ ክልል ምስራቃዊ አካባቢዎች መውጣቱን ጠቅሰው፥ በዘመቻው ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያውያን አሸናፊ ሆነዋል ነው ያሉት።

በዚህ ዘመቻ ወራሪው ሀይል እንዲበታተን እና እንዲደመሰስ በማድረግ ሳይወሰን ተደናብሮ ይዞ የገባውን ተተኳሽ እና ራሱን ይዞ እንዳይወጣ ወይም እንዲደመሰስ አልያም ሳይወድ በግድ እጁን እንዲሰጥ ያስገደደ ታላቅ ዘመቻ ነበር ብለዋል።

በዘመቻው የመከላከያ ሰራዊት አባላት ታላቅ ጀብዱ የሰሩበትና በታሪክ ወርቃማ ሆኖ የሚጻፍ ስራ የሰሩበት መሆኑንም ገልጸዋል።

የአማራ እና አፋር ክልል የፀጥታ ሃይሎችም የራሳቸውን ጥረት አድርገው አኩሪ ድርሻ የተወጡበት መሆኑን ጠቅሰዋል።

አሁን ላይ የጠላት መሻት፣ ፍላጎትና የማድረግ አቅም ክፉኛ ተመቷል ያሉት ሚኒስትሩ፥ ይሁን እንጂ የጠላት ሃይል ፍላጎት ዳግም እንዳይቀሰቀስ መንግስት በቀጣይ በጥናት ላይ ተመስርቶ እርምጃ ይወስዳል ብለዋል።

የወገን ሃይል እና ደጀኑ አሁን ያሉበትን የአሸናፊነት ቁመና በመጠበቅና ጥንካሬያቸውን ይዘው እንዲቀጥሉ ጠንካራ ስራ እንደሚሰራ በመጥቀስም፥ ህብረተሰቡም እስከ ዛሬ ሲያደርግ የነበረውን ድጋፍ አጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ብለዋል ሚኒስትሩ በመግለጫቸው።

ወራሪውን ሃይል በገባበት የደመሰሰው የመከላከያ ሰራዊትም አሁን ባለበት ቦታ አፅንቶ እንዲቆይ ታዟልም ነው ያሉት።

ለዚህም ከዚህ ቀደም በትግራይ ክልል ካጋጠሙ ችግሮች መማር አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ፣ በሽብር ቡድኑ ሴራና ወጥመድ ላለመግባት እና የመከላከያ ሰራዊት የሀገርን የግዛት አንድነት እና ሰላምን ለአደጋ የሚዳርግ ሁኔታ ተፈጥሯል ተብሎ በሚታሰብበት በማንኛውም ቦታ፣ ጊዜና ሁኔታ በተጠና መልኩ እርምጃ የሚወስድ በመሆኑ መወሰኑን አስረድተዋል።

በምዕራብ አማራ ካለው ሁኔታ ጋር በተያያዘም መንግስት ወደፊት መረጃዎችን እንደሚሰጥ ጠቁመዋል።

በኦሮሚያ ክልል በንጹሃን ላይ በአሸባሪው ሸኔ የሚፈጸሙ ጥቃቶችን ለመከላከል መንግስት አስፈላጊውን እርምጃ እንደሚወስድም ነው ያረጋገጡት።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.