Fana: At a Speed of Life!

ከፌደራልና አዲስ አበባ ሆስፒታሎች ጋር ትስስር በመፍጠር በህወሃት ዝርፊያና ውድመት የደረሰባቸው 11 ሆስፒታሎች አገልግሎት እንዲጀምሩ ተደርጓል

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 14፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የጤና ሚኒስቴር የፌደራል ሆስፒታሎች እና የአዲስ አበባ ጤና ቢሮን በአሸባሪው ህወሓት ከወደሙ የጤና ተቋማት ጋር በማስተሳሰር የድጋፍ ጥምረትን ዘርግቷል፡፡

በአገራዊ ወቅታዊ የጤና ጉዳዮች ላይ የጤና ሚኒስቴሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡

በመግለጫቸውም አሸባሪው ህወሓት ወርሮ ይዟቸው በነበሩ የአማራ እና አፋር ክልሎች የተለያዩ ጥፋቶችን ማድረሱ ተነስቷል፡፡

በዚህም የጤና ተቋማት ተዘርፈዋል ፤ ወድመዋልም ነው ያሉት የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ በመግለጫቸው ፡፡

በአማራ ክልል 41 ሆስፒታሎች፣ 453 ጤና ጣቢያዎች፣ 1850 ጤና ኬላዎች ፣ በአፋር ክልል 1 ሆስፒታል ፣ 19 ጤና ጣቢያዎች እና 374 ጤና ኬላዎች ጉዳት የደረሰባቸው ሲሆን፥ በዚህም አገልግሎት መስጠት እንዳቋረጡ ሚኒስትሯ አንስተዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ በኦሮሚያ፣ በቤንሻንጉል ጉሙዝም በግጭት ምክንያት አገልግሎት ያቋረጡ ጤና ተቋማት እንዳሉም ተረጋግጧል፡፡

የጤና ሚኒስቴር እነዚህ ከፍተኛ ውድመትና ዝርፍያ የደረሰባቸውን የጤና ተቋማት ለማቋቋምና የጤና አገልግሎትን ደረጃ በደረጃ ለማስጀመር እንዲቻል ዘርፈ ብዙ የስራ እቅስቃሴዎች እንደጀመረ ነው የገለፁት፡፡

በዚህም የጤና ሚኒስቴር የአዲስ አበባ ጤና ቢሮና የፌዴራል ሆስፒታሎችን ከወደሙ ሆስፒታሎች ጋር በማስተሳሰር የድጋፍ ጥምረት በመዘርጋት አስፈላጊውን የሰው ሀይል፣ የመድኃኒት እና የህክምና መሳርያዎች ድጋፍ እንዲያደርጉ ሰፊ ስራ መጀመሩን አመልክተዋል።

በቀጣይም ሌሎች ክልሎች እና ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታሎችን በማስተባበር ድጋፉ በስፋት እንደሚቀጥል ተገልጿል።

በአጠቃላይ በግጭቱ ጉዳት ከደረሰባችው 34 የሚሆኑ ሆስፒታሎችን ከፌዴራል ሆስፒታሎች፣ ከአዲስ አበባ ጤና ቢሮ ስር ከሚገኙ ሆስፒታሎች እና ከዩኒቨርስቲ ሆስፒታሎች ጋር እንዲሁም 69 የወደሙ ጤና ጣቢያዎችን ደግሞ ከክልል ጤና ቢሮዎች እና ከግል ጤና ተቋማት ህብረት ጋር በማጣመር በፍጥነት አገልግሎት እንዲጀምሩ ለማድረግ ሰፊ ስራዎች እየተሰሩ እንደሚገኙ ተነግሯል፡፡

በዚህ መሰረት ባለፉት ሁለት ሳምንታት ውስጥ ከፌዴራል ሆስፒታሎችና የአዲስ አበባ ሆስፒታሎች ጋር በተፈጠረው ትስስር በተሰሩ ስራዎች 11 ሆስፒታሎች ድንገተኛ እና መሰረታዊ የጤና አገልግሎት መስጠት የጀመሩ ሲሆን ፥ 14 የሚሆኑት ደግሞ አገልግሎት እንዲጀምሩ በሚያስችል ደረጃ ዝግጁ ተደርገዋልም ተብሏል፡፡

የተቀሩት ሰባት የሚሆኑት ደግሞ በቀጣይ ጥቂት ቀናት ውስጥ ስራ የሚጀምሩ ይሆናል፡፡

የወደሙ ጤና ጣቢያዎችንም መልሶ በማደራጀት ድንገተኛ እና መሰረታዊ የጤና አገልግሎት የጀመሩበት ሁኔታዎች መፈጠራቸውም ተጠቁሟል፡፡

በአማራና አፋር ክልሎች በ64 ጤና ጣቢያዎች መደበኛ የጤና አገልግሎት ማስጀመር መቻሉም ተነስቷል፡፡

በአምቡላንሶች መጎዳት የሚፈጥረውን ጫና ታሳቢ በማድረግ ከዚህ ቀደም ከተደረገው የአምቡላንስ ድጋፍ በተጨማሪ 13 አምቡላንሶችን ጦርነቱ ወደ ተከሰተባቸው አካባቢዎች ማሰራጨት መቻሉም ነው በመግለጫው የተመለከተው፡፡

በተጨማሪም ከዚህ በፊት በተለያዩ ብልሽት ቆመው ከነበሩ ወደ 114 አምቡላንሶች 64ቱ ተጠግነው ለአገልግሎት ዝግጁ ሆነዋል፡፡

በቀጣይም ሁሉንም ጤና ተቋማትን በሙሉ አቅማቸው ከዚህ በፊት ከነበረው አጋልግሎት በተሻለ ደረጀ መስጠት እንዲችሉ ሁሉንም ባለድርሻ አካላት ያሳተፈ እንቅስቃሴ መጀመሩንም ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

አካባቢዎን ይጠብቁ!
ወደ ግንባር ይዝመቱ!
መከላከያን ይደግፉ!

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.