Fana: At a Speed of Life!

አሸባሪው ህወሓት በቆቦ አካባቢ በወረራ በቆየባቸው ጊዜያት ከ600 በላይ ንጹሃንን ገድሏል – ነዋሪዎች

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 15፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) አሸባሪው ህወሓት በሰሜን ወሎ ዞን ቆቦ አካባቢ በወረራ በቆየባቸው ጊዜያት ከ600 በላይ ንጹሃንን መግደሉንና በአንድ ቀንም 89 ንጹሃንን ገድሎ በጅምላ መቅበሩን የአካባቢው ነዋሪዎች ተናገሩ።
የሟች ቤተሰቦችም አስከሬን እንዳያነሱና እርማቸውን እንዳያወጡ በመከልከል ይቅር የማይባል ግፍ መፈጸሙንም ገልጸዋል።
የከተማዋ ነዋሪዎች እንደገለጹት፥ በከተማው በሦስት ዙር ከተደረገው ውጊያ የበለጠ የሚከፋው የራያ አርበኞች፣ ሚሊሻና ታጣቂዎች የሽብር ቡድኑን ለመከላከል ጳጉሜን 4 ቀን 2013 ዓ.ም ባደረጉት ከፍተኛ ተጋድሎ፥ ቂም የያዘው ቡድኑ በየአካባቢው ያገኘውን አርሶ አደር፣ ወዛደር፣ እናቶችን ማንነትን መሰረት አድርጎ መጨፍጨፉን ተናግረዋል።
በአጠቃላይ በወረራ በቆየባቸው ጊዜያት 600 የሚደርሱ ንጹሃን መቀበራቸውንም ተናግረዋል።
በቆቦ ከተማ ብቻ ጳጉሜን 5 ቀን 2013 ዓ.ም አሸባሪው ሕወሓት የጨፈጨፋቸው 89 ንጹሀን ዜጎች በጅምላ መቀበራቸውን አመልክተዋል።
በማግስቱ የዘመን መለወጫ ዕለትም 16 ንጹሀን ተቀብረዋል። ይህ አሀዝ በአካባቢው ገጠር ቀበሌዎች የተቀበሩትንና የተሰወሩትን እንደማያካትትም ነዋሪዎቹ ጠቁመዋል።
ሦስት የቤተሰባቸው አባል የተገደሉባቸው ነዋሪ እንደገለጹት፥ በዕለቱ በአካባቢያቸው ከፍተኛ የተኩስ እሩምታ ይሰማ ነበር።
ምሽት 11:00 ሰዓት ገደማ ቤት ውስጥ በመግባት ሰባት ሆነው ተሸሽገው ከነበሩት ህጻናትን ትተው አራቱን እንደወሰዷቸው ተናግረዋል።
“እባካችሁ አትውሰዷቸው፣ ገበሬ ናቸው የሚያውቁት ነገር የለም ብላቸውም ተጠይቀው ይመለሳሉ” በማለት እየገፈተሩና እየተቆጡ እንደወሰዷቸው፣ አንደኛውን ክንዱን መትተውት ቆስሎ መመለሱን አስታውሰዋል።
“በነጋታው ማለዳ ተነስቼ ፍለጋ ወጣሁ ከእኔ ቤተሰቦች ጭምር አራት ሰዎች አንድ ቦታ ተገድለው አገኘኋቸው፤ ነጠላ አለበስኳቸው፤ ተደፍቼ አለቀስኩ” ብለዋል።
አንቺንም እንዳንገድልሽ ዝም በይ በማለት እንዳስፈራራቸው ጠቁመዋል።
እኔንም ግደለኝ ቢሉም በማመናጨቅና በመገፈታተር እንዳባረራቸው ይናገራሉ።
አስከሬኖቹ ጸሃይ ላይ ውለው አድረው ሽማግሌ ተልኮ ሳያለቅሱ እንዲያነሱ እንደተፈቀደ ተናግረዋል።
ሁለት ወንድሞቻቸውና የእህታቸው ባለቤት የተገደሉባቸው ነዋሪ እንዳሉት፥ አስከሬን ከወደቀበት ያነሱት ሽማግሌ ልከው መሆኑን፣ በኬሻ ጠቅልለው አስክሬኖቹን ሳያጥቡ መቅበራቸውን ገልጸዋል።
በዕለቱ ጉድጓድ የሚቆፍር ጠፍቶ ብዙዎችን እየደራረቡ ሲቀበሩ መመልከታቸውን፣ እንዳያለቅሱ መከልከላቸውን በመጠቆምም፥ ምሽት ቤት እያንኳኩ ሲያስቸግሯቸውም ጥለው ወደ ገጠር መሰደዳቸውን ተናግረዋል። ሲመለሱም ቤታቸው ተዘርፎና ወድሞ እንዳገኙት አመልክተዋል።
የተጎጂዎቹ ጎረቤትም አራት ልጆች አንድ ቦታ መገደላቸውን እንደተመለከቱ ተናግረዋል።
አሸባሪ ቡድኑ ለቅሶ ስለከለከለ አስከሬኖቹ ሳይታጠቡና አስፈላጊው የሃዘን ስነ-ስርዓት ሳይደረግላቸው በኬሻ ጠቅልለው ለቀብር እንደወሰዷቸው መስክረዋል ሲል የዘበው ኢፕድ ነው።
አካባቢዎን ይጠብቁ!
ወደ ግንባር ይዝመቱ!
መከላከያን ይደግፉ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.