Fana: At a Speed of Life!

ህይወቱን ለሀገሩ የሰጠና ወራሪ ቡድኑን የመከተ ህዝብ የወደሙ ንብረቶችን ለማቋቋም አይሳነውም- የአማራና ኦሮሚያ ክልሎች ከፍተኛ አመራሮች

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 15፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ህይወቱን፣ አካሉን ለሀገሩ የሰጠ እና ወራሪ ቡድኑን የመከተ ህዝብ የወደሙ ንብረቶችን ለማቋቋም አይሳነውም ሲሉ የአማራና ኦሮሚያ ክልሎች ከፍተኛ አመራሮች ገለጹ፡፡

አሸባሪው የህወሓት ቡድን የውሃና የጤና ተቋማትን፣ የህብረት ስራ ማህበራት ንብረቶችንና ሌሎች ማህበራዊ አገልግሎት መስጫ ተቋማትን ማውደሙን እና ዘርፎ መውሰዱን የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ የፖለቲካ ዘርፍ ሀላፊ አቶ ሞላ መልካሙ ተናግረዋል፡፡
ከኢትዮጵያ መዳከም እናተርፋለን ብለው የሚያስቡ አንዳንድ ምዕራባውያን መኖራቸውን የገለጹት ሃላፊው፥ ትልቁ ፕሮጀክት እና ግብ ኢትዮጵያን ማፍረስና መበታተን እንደሆነ ይናገራሉ፡፡

ይሄንን የውጭ ጫናና የአሸባሪ ቡድኑን ወረራ በኢትዮጵያ ህዝብ ደጀንነት እና በተቀናጀ ስምሪት መመከት ተችሏል ነው ያሉት፡፡

የተዘረፉና የወደሙ ንብረቶችን የመለየት ስራ ሰፊ ጊዜ እንደሚጠይቅና ሂደት ላይ መሆኑን የገለጹ ሲሆን፥ የወደሙ ተቋማትን በተመሳሳይ በህዝብ ርብርብ መልሶ ማቋቋም እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል፡፡

ውድመቶችንና የተፈጸመውን ግፍ የክልሉ ህዝብ ብቻ ሳይሆን ሁሉም ኢትዮጵያዊ ማየት እንዳለበት ጠቅሰው፥ ያልተገለጹ ለሚዲያ የማይመጥኑ የአሸባሪው ቡድን እኩይ ድርጊቶችም አሉ ብለዋል፡፡

አሸባሪዎቹ ህወሓት እና ሸኔ በሚያደርጉት እኩይ ተግባር ንጹሃን ዜጎች መገደላቸውን እና ብዙዎች መፈናቀላቸውን የተናገሩት ደግሞ የኦሮሚያ ክልል አደጋ ስጋት ስራ አመራርና የልማት ተነሺ ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ሙስጠፋ ከድር ናቸው፡፡

በእነዚህ ቡድኖች ላይ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ትግል እና ተቃውሞ ማድረግ እንዳለበት ሃላፊው ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር በነበራቸው ቆይታ አሳስበዋል፡፡

ኦነግ ሸኔ የማህበረሰቡን አሴት በመድፈር ጭምር በተለይ በደቡብ እና ምዕራብ አካባቢ በሚገኙ የኦሮሚያ ክልል ዞኖች ላይ በህብረተሰቡ ላይ ጥቃት እያደረሰ እንደሚገኝ ጠቅሰው፥ በሰሜኑ የተወሰደው እርምጃ ሸኔ ላይም እንደሚደገም ኮሚሽነሩ ገልጸዋል፡፡

“ትልቁ ነገር የውስጣችን ጥንካሬ ነው፣ ከሰራን እናመርታለን፣ ከተባበርን እናሸንፋለን” ያሉት ኮሚሽነሩ፥ የተፈናቀሉ ወገኖችን መርዳት እና በአሸባሪው ቡደን የወደሙ ተቋማትን መልሶ መገንባት ይኖርብና ልብለዋል፡፡

አካባቢዎን ይጠብቁ!
ወደ ግንባር ይዝመቱ!
መከላከያን ይደግፉ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.