Fana: At a Speed of Life!

በወራሪው ቡድን ተይዘው የነበሩ አካባቢዎችን በአኩሪ ሁኔታ ነጻ ማድረግ ተችሏል – የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 16፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የሽብር ቡድኑ ይዟቸው የነበሩ አካባቢዎች ነጻ መሆናቸውን ተከትሎ ዜጎችን ወደ ቀያቸው ለመመለስ እየተሰራ መሆኑን የመንግስት ኮሚኒኬሽን አገልግሎት ገለፀ።
የመንግስት ኮሚኒኬሽን አገልግሎት የሚኒስትር ዴኤታ ሰላማዊት ካሳ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ መግለጫ ሰጥተዋል።
በወራሪው ቡድን ተይዘው የነበሩ አካባቢዎችን በአኩሪ ሁኔታ ነጻ ማድረግ መቻሉን ነው በዚሁ ወቅት ያመለከቱት።
በሽብር ቡድኑ የደረሱ ሰብዓዊ እና ቁሳዊ ጉዳቶችን የሚያጠና የወንጀል ምርመራ እና የማስቀጣት ቡድን ወደ ስፍራው መላኩንም አንስተዋል፡፡
በሽብር ቡድኑ የንጹሀን ዜጎች ህይወት መጥፋትን፣ የአካል መጉደልን፣ የአስገድዶ መድፈር ወንጀልን ፣ የቤት ንብርት መፈናቀልን፣ የንብረት ውድመት፣ መንግስታዊ ተቋማት ሰነዶችን መጥፋት እንደዚሁም እጅግ ዘግናኝ ወንጀሎች ሲፈጸሙ እንደነበር ይታወቃል ብለዋል፡፡
እንደ ሚኒስትር ዴኤታዋ እነዚህን ሁሉ ወንጀሎች ለማጣራት በሚያስል ሁኔታ ነው ቡድኖች የተሰማሩት፡፡
በመግለጫቸው በዚህ ወረራ ወቅት የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን እና የንብረት ውድመትን ያደረሱ ጥፋተኛ ግለሰቦችንም ወደ ህግ በማቅረብ ፍትህ የማሰጠት ስራው እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።
በሌላ በኩል ሚኒስትር ዴኤታዋ፥ በአማራ እና በአፋር ክልሎች አጣሪ ቡድን ተልኮ ሥራ መጀመሩንም አንስተዋል፡፡
በዚሁ መሠረትም በአፋር ክልል በሥሩ ሁለት ንዑሳን ቡድኖችን ያካተተ አንድ አጣሪ ቡድን ተልኮ እየመረመረ ይገኛል ብለዋል፡፡
ይህም በተለያየ መልኩ ምርመራቸውን እያደረጉ የተጠናቀረ ትክክለኛውን ስዕል በሚያሳይ መልኩ መረጃ ለማቅረብ እንደሚያስችል አመላክተዋል፡፡ ተጠያቂ የሚሆኑ አካላትንም በዚያው ልክ ተጠያቂ ለማድረግ እንዲቻል ይደረጋልም ነው ያሉት፡፡
በአማራ ክልል ደግሞ በርከት ያሉ ቡድኖች መሰማራታቸውን ጠቁመው፥ ከሥር ከሥር ነጻ የሚወጡ አካባቢዎችንም ምልከታዎችን ማድረግ በሚያስችላቸው መልኩ እንደተሰማሩ ጠቁመዋል።
በዋናነት ሸዋ ሮቢትን ጨምሮ በሰሜን ሸዋ ስር በሚገኙ አሥር ወረዳዎች ላይ፣ በደቡብ ወሎ የሚገኙ ስምንት ወረዳዎች ላይ ፣ የኦሮሞ ብሔረሰብ ልዩ ዞን፣ በደሴና ኮምቦልቻ እንዲሁም ጋሸናን ጨምሮ ደግሞ በሰሜን ወሎ ዞን ሥር ያሉ ወረዳዎችን ምርመራ ለማድረግ እነዚህ ቡድኖች ተሰማርተው ምልከታዎችን እያደረጉ ነው፡፡
እነዚሁ ቡድኖች ወደ ዋግኽምራና ወልዲያ ሄደውም ምልከታ ማድረግ ጀምረዋል ነው ያሉት፡፡
በአጠቃላይ ምርመራዎቹ የሚካሄዱት በአሸባሪው ቡድን የደረሰውን ጥፋት ማሳየት በሚያስችል መልኩ በምልከታውና በምርመራው የሚገኙ ውጤቶችም በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት ሊኖራቸው በሚችል ደረጃ እንዲሆን በዓለም አቀፍ ደረጃ የተቀመጡ የጦር ወንጀል ምርመራ መስፈርቶችን ባሟላ መልኩ የሚካሄዱ ይሆናሉ ብለዋል፡፡
ሚኒስትር ዴኤታዋ በመግለጫቸው እንዳመላከተቱት፥ ከአማራ እና አፋር ክልሎች ወደ 2 ሚሊየን የሚሆኑ ዜጎች በጦርነቱ ምክንያት መፈናቀላቸውን አንስተዋል፡፡
ከእነዚህ ውስጥ 151 ሺህ የሚሆኑት ዜጎች በክልሎቹ ውስጥ በተቋቋሙ ወደ 25 የሚሆኑ የጋራ መጠለያዎች/የጋራ ቦታዎች/ ይኖራሉ፤ ሌሎቹ ከ90 በመቶ በላይ የሚሆኑት ግን በተቀባይ ማህበረሰብ ውስጥ የሚገኙ ናቸው ብለዋል፡፡
አብዛኞቹ ተፈናቃዮችም በሰሜን ጎንደር እንደሚገኙ መረጃዎች ያመላክታሉ ያሉት ዴኤታዋ፥ በደሴ፣ በሰሜን ሸዋ እና በምዕራብ ጎጃም እንደዚሁ በስፋት ተፈናቃዮች መኖራቸውን አንስተዋል፡፡
በሽብር ቡድኑ በርካታ የጤና ተቋማት መውደማቸውን ገልጸው፥ ለተፈናቃዮች መሠረታዊ የጤና አገልግሎት ለማቅረብም በጤና ሚኒስቴር እና በተለያዩ አጋር ተቋማት ትብብር በርካታ ስራዎች መሠራታቸውን አብራርተዋል፡፡
በተለይ በጤናው ዘርፍ የጤና ተቋማትን መልሶ በማቋቋም ረገድ በአጭር ጊዜ ለማጠናቀቅ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ገልጸው፥ ከ35 በላይ ሆስፒታሎች፣ 418 ጤና ጣቢያዎች፣ 1 ሺህ 700 በላይ ጤና ኬላዎች በአሸባሪው ቡድን መውደማቸውን አመልክተዋል፡፡
ተማሪዎችን በፍጥነት ወደ ትምህርት ገበታቸው ለመመለስ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች እየተሰሩ መሆናቸውንም በመግለጫቸው አንስተዋል፡፡

በዮሐንስ ደርበው

አካባቢዎን ይጠብቁ!
ወደ ግንባር ይዝመቱ!
መከላከያን ይደግፉ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.