የሀገር ውስጥ ዜና

በመዲናዋ መንገድ ለሰው ከትራፊክ ፍሰት ነፃ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ተካሄደ

By Meseret Awoke

December 26, 2021

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 17፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባ መንገድ ለሰው ከትራፊክ ፍሰት ነፃ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ እና የእግር ጉዞ ፕሮግራም ተካሄደ፡፡

በመርኃ ግብሩ ጤናማ ማህበረሰብና ስፖርታዊ እንቅስቃሴን ባህሉ ያደረገ ዜጋን መገንባት የሚያስችል ተግባራቶች እየተከናወኑ እንደሚገኙም ተገልጿል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ከአዲስ አበባ ከተማ ትራፊክ ማኔጅመንት ኤጀንሲ ጋር በመተባበር ነው መንገድ ለሰው በሚል መሪ ቃል በርካታ የከተማውን ነዋሪዎች ያሳተፈ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ እና የእግር ጉዞ የተካሄደው፡፡

መነሻውን ከፒያሳ በማድረግ ወደ መስቀል አደባባይ በሚወስደው መንገድ በተካሄደዉ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ እና የእግር ጉዞ የአካባቢውን ማህበረሰብ፣ የስፖርት ለሰላም ማህበር አባላት፣ የስፖርት ክለብ ደጋፊዎች፣ የማርሻል አርት ቤተሰቦች፣ ብስክሌተኞች፣ ስኬተሮችን ጨምሮ የከተማው የስፖርት ቤተሰቦችና አመራሮች ተሳትፈዋል፡፡

በፕሮግራሙ ላይ የተገኙት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ሃላፊ አቶ አብርሀም ታደሰ ፥ ይህ መንገድ ለሰው የአካል ብቃት እንቅስቃሴ መርሃ ግብር በየሳምንቱ ተጠናክሮ በሁሉም አካባቢዎች እንደሚቀጥል ተናግረዋል፡፡

በመርሃግብሩ ላይ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል በልዩ ልዩ ፕሮግራሞች ላይ በመሳተፍ እና ጤናውን በመጠበቅ ንቁና አምራች ዜጋ እንዲሆን አቶ አብርሃም መልዕክት ማስተላለፋቸውን ከከተማው ፕሬስ ሴክሬታሪ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

አካባቢዎን ይጠብቁ! ወደ ግንባር ይዝመቱ! መከላከያን ይደግፉ!

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!