Fana: At a Speed of Life!

ሕዝቡ ከሐዘን ወጥቶ ለትውልድ የሚተርፍ የጀግንነት ሥራ እንዲከውን ርእሰ መስተዳድር ዶክተር ይልቃል ከፋለ አሳሰቡ

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 17፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የአማራ ክልል ርእሰ መስተዳድር ዶክተር ይልቃል ከፋለ እና የክልሉ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች በወልድያ ከተማ ተገኝተው ከሰሜን፣ ከደቡብና ከኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳድር አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል ከብፁዕ አቡነ ኤርሚያስና ከሌሎች የሃይማኖት አባቶች ጋር ተወያይተዋል።

ለቂ ጳጳስ አቡነ ኤርሚያስ አካባቢው በወራሪውና አሸባሪው ቡድን ተይዞ በነበረበት ወቅት በርካታ ሕዝብ የማዳን ሥራዎችን ሠርተዋል።

በከተማዋ የሚገኙ የእስልምና አባቶችም ከአቡነ ኤርሚያስ ጋር በመሆን ከፍተኛ ሥራዎችን ከውነዋል።

የሃይማኖት አባቶቹ ሕዝብን በመጠበቅ እና በችግር ቀን በመድረስ የመከራውን ቀን አሳልፈዋል።

ርእሰ መስተዳድር ዶክተር ይልቃል ከፋለ እና ሌሎች የክልሉ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎችም የሃይማኖት አባቶችን በወልድያ ከተማ ተገኝተው አመስግነዋል ።

አሸባሪውን ትህነግ ለመደምሰስ በነበረው ትግል ጉዳት የደረሰባቸው የወገን ጦር አባላት በአቡነ ኤርሚያስ አማካኝነት ከፍተኛ እንክብካቤ ሲደረግላቸውም መቆየቱንም ገልጸዋል።

ብፁዕነታቸው ከቆሰሉበት ወስደው ለወራት በመንከባከብ ከሞት እንዳተረፏቸውም አብራርተዋል።

የሠራዊቱ አባላት አቡነ ኤርሚያስ ለሕዝቡ ብቻ ሳይሆን ጉዳት ለደረሰባቸው የሠራዊት አባላት የክፉ ቀን አባት መሆናቸውን ነው የተናገሩት።

በብፁዕ አቡነ ኤርሚያስ ድጋፍ ወደ ጤንነታቸው የተመለሱት የወገን ጦር አባላትም ግንባር ለመሰለፍ ዝግጁነታቸውን ገልጸዋል።

ርእሰ መስተዳድሩ አቡነ ኤርሚያስ ተቀብለው ያስታመሟቸውን የወገን ጦር አባላትን ሲጠይቁ ÷ ምንም እንኳን ደም ብታፈሱም ዓላማችሁ ተሳክቷል ብለዋቸዋል።

አቡነ ኤርሚያስ ለተጎዳ ሕዝብ የቆሙ መሆናቸው እናንተ ማሳያዎች ናችሁም ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ለተቸገሩት በመድረስ፣ በማሰባሰብ፣ ሰላምና ደኅንነት እንዲጠበቅ በማድረግ፣ የወደቁትን በመንከባከብ አርዓያ የሚሆን ተግባር ፈፅማለች ነው ያሉት።

አቡነ ኤርሚያስ ሰውን አሰባስበው መከራውን እንዲያልፍ ያደረጉ እውነተኛ አባት መሆናቸውንም ገልፀው ÷ ለሠሩት ሥራ ክብርና ምስጋና አለንም ብለዋል።

ሰዎች ነፃነት እና ክብር ያስፈልጋቸዋል ያሉት ርእሰ መስተዳድሩ ÷ የአማራ ሕዝብ ከፍተኛ ጉዳት ደርሶበታል ፤ ነገር ግን የአማራ ሕዝብና መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ መዘጋጀት ያለበት ዳግም ጥቃት እንዳይደርስ ምን እናድርግ በሚለው ላይ ነው ብለዋል።

የወደመው ሀብት ከነፃነት እንደማይበልጥም ገልፀዋል።

ይህም ከነበረው በበለጠ ካልሆነም በነበረው እንደሚገነባ ገልጸው ÷ ሕዝቡ ከሐዘን ወጥቶ ለትውልድ የሚተርፍ የጀግንነት ሥራ እንዲሠራም አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ኢትዮጵያን የሚያስጣራ ቅርስና እሴት ያላት መሆኗን ያነሱት ርእሰ መስተዳድሩ ÷ ታላቅ አሻራ ያላት ተቋም ናትም ብለዋል።

በችግር ጊዜ ሕዝብ የምታፅናና ከችግር የምታሻግር መሆኗን በተግባር ያሳየች ናት ብለው ÷ አቡነ ኤርሚያስ ሕዝብን አንድ አድርገው ችግሩን እንዲያልፍ ማድረጋቸውንም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን መገለጫዋ የአቡነ ኤርሚያስ ሥራ መሆኑንም ተናግረዋል።

ሕዝብ በችግር እንዴት ያልፋል የሚለውን ማስተማራቸውንም አንስተዋል።

የሰሜን፣ የደቡብ ወሎና የኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ኤርሚያስ በሃይማኖት ብንለያይ ሰውን በማትረፍ ግን አንለያይም ብለዋል።

ይህ በአፍ ብቻ ሳይሆን በተግባር ታይቷልም ነው ያሉት።
የክርስትና ሃይማኖት ከእስልምና ሃይማኖት አባቶች ጋር በመሆን በጋራ መስራታቸውንም ገልፀዋል።

የወልድያ ከተማ አስተዳደር የሰላም የመስጊድ ኮሚቴ አባል ሀጂ ያሲን እንድሪስ ÷ የችግሩ ጊዜ ከአጋጠመን ክፋት አንድ የሆንበት ይበልጥብኛል ብለዋል።

ከችግሩ የበለጠ አንድ ሆነንበታል ብለው ÷ በአንድነት በጋራ መወጣታቸውንም ገልፀዋል።

አንድነታችን አጠናክረን መሄድ አለብን ያሉት ሀጂ ያሲን ÷ በአንድነት ወደፊት ለሚመጣው ችግር መዘጋጀትና ይገባልም ብለዋል።

በዚህ አንድነት መቀጠል ከተቻለ ሊመጣ የሚችለውን ጠላት ማሸነፍ እንደሚቻልም ገልፀዋል።

ርእሰ መስተዳድሩ ዶክተር ይልቃል ከፋለ እና የክልሉ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች የወልድያ ዩኒቨርሲቲን ጨምሮ በከተማዋ የወደሙ ተቋማትን መመልከታቸውንም አሚኮ ዘግቧል።

አካባቢዎን ይጠብቁ!
ወደ ግንባር ይዝመቱ!
መከላከያን ይደግፉ!

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.