Fana: At a Speed of Life!

በጦርነትና በግጭት ጉዳት ለደረሰባቸው ዜጎች መልሶ ማቋቋም የ5 ቢሊዮን ብር ተጨማሪ በጀት ተዘጋጀ

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 18፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በጦርነትና በግጭት ጉዳት ለደረሰባቸው ዜጎች መልሶ ማቋቋሚያ የሚውል የአምስት ቢሊዮን ብር ተጨማሪ በጀት መዘጋጀቱን የገንዘብ ሚኒስትር አቶ አህመድ ሺዴ ገለጹ፡፡

በገንዘብ ሚኒስቴር የሚመራው የመልሶ ማቋቋም ሴክሬታሪያት ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ታህሳስ 15 ቀን 2014 ዓ.ም በገንዘብ ሚኒስቴር የመሰብሰቢያ አዳራሽ የመጀመሪያውን ውይይት ባደረገበት ወቅት አቶ አህመድ እንደገለጹት፥ በገንዘብ ሚኒስቴር የተዘጋጀው የ5 ቢሊዮን ብር ተጨማሪ በጀት ለሚኒስትሮች ምክር ቤት መቅረቡን ጠቁመው ተጨማሪውን በጀት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዳጸደቀው በቀጥታ ወደ ስራ እንደሚገባ አመልክተዋል፡፡

መንግስት ከሚመድበው መነሻ በጀት በተጨማሪም ከልማት አጋሮች በተለይም ከአለም ባንክ ለመልሶ ማቋቋሙ ከፍተኛ የገንዘብ ድጋፍ እንደሚጠበቅ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ገልፀዋል።

የመልሶ ማቋቋሙ መርሀ ግብሩ በመንግስት የሚመራ፣ የተቀናጀ፣ በየደረጃው በፕሮግራም ተግባራዊ የሚደረግ፣ ተጠያቂነት ያለውና ዘላቂ መፍትሄ ለማምጣት የሚተጋ መሆኑንም ነው ያስረዱት፡፡

በጦርነቱና በግጭቱ የደረሰውን ጉዳት ለማውቅና በገንዘብ ለመተመን የሚያስችል የዳሰሳ ጥናት ለማድረግ የሚያስችል የመነሻ ሀሳብ በገንዘብ ሚኒስቴር ተዘጋጅቶ ለመልሶ ማቋቋም ሴክሬታያት ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት ቀርቧልም ነው ያሉት።

የኮሚቴ አባላትም የመልሶ ማቋቋም መርሀግብሩ ከሰሜኑ የሀገራችን ክፍሎች በተጨማሪ በሌሎች ክልሎች በግጭት የተፈናቀሉትንም እንዲያካትት፣ የሀብት አሰባሰብ ድግግሞሽ እንዲወገድና በአንድ ቋት እንዲሰባሰብ፣ ክልሎች ንቁ ተሳትፎ የሚደርጉቡት ምቹ ሁኔታ እንዲመቻች፣ ከሌሎች መሰል ብሄራዊ ኮሚቴዎች ጋር በቅንጅት እንዲሰራና የግሉን ዘርፍና ዲያስፖራውን እንዲያሳትፉ አስተያየት ሰጥተዋል፡፡

በውይይቱ የመልሶ ማቋቋም ሴክሬታሪያቱ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት የሆኑት የትምህርት፣ የጤና፣ የፕላንና ልማት፣ የውሃና ኢነርጂ፣ የኢንዱስትሪ፣ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ፣ የስራና ክህሎት፣ የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስትሮችና ሌሎች ጉዳዩ የሚመለከታቸው የፌዴራል መስሪያ ቤት አመራሮች መገኘታቸውን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

አካባቢዎን ይጠብቁ!
ወደ ግንባር ይዝመቱ!
መከላከያን ይደግፉ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.