Fana: At a Speed of Life!

በአማራ ክልል ከ80 ሺህ ሄክታር በላይ ማሳ የስንዴ ሰብል በመስኖ ይለማል – የክልሉ ግብርና ቢሮ

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 18፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) አሸባሪው የህወሓት ቡድን በግብርናው ዘርፍ ባደረሰው የኢኮኖሚ ውድመት ምክንያት በሚሊየን የሚቆጠሩ ዜጎች የርሃብ አደጋ ተጋርጦባቸዋል።
ችግሩን ለመቅረፍ የሚያስችል የመስኖ ልማት በሁሉም አካባቢዎች በሰፊው እንደሚከናወን የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ አስታውቋል፡፡
የቢሮው ምክትል ሃላፊ ቃልኪዳን ሽፈራው በሰሜን ሸዋ ዞን አንጾኪያ ገምዛ ወረዳ በተካሄደ የመስኖ ልማት ንቅናቄ መርሃግብር ላይ ተገኝተው÷ ስንዴን በመስኖ በማልማት በአሸባሪው የጥፋት ሃይል የደረሰውን ውድመት ከማካካስ ባሻገር በስንዴ እርዳታ ስም በሀገራችን ላይ የሚደርሰውን ጣልቃ ገብነት ማስቀረት አለብን ብለዋል።
በክልሉ እስካሁን 17 ሺህ ሄክታር ማሳ በስንዴ የመስኖ ልማት ተሸፍኗል ያሉት አቶ ቃል ኪዳን÷ ከ80 ሺህ ሄክታር በላይ ማሳ ስንዴን በመስኖ በማልማት ከ3 ነጥብ 5 ሚሊየን ኩንታል በላይ ምርት ለማግኘት እንደሚሰራ ገልጸዋል።
የመስክ ምልከታ በተካሄደባቸው የአንጾኪያ ገምዛ ቀበሌዎች በመስኖ የለማ የስንዴ ቡቃያ የክልል፣ የዞንና የወረዳ አመራሮች በተገኙበት ተጎብኝቷል።
ስንዴን በመስኖ የሚያለሙ የወረዳው አርሶ አደሮች ለደብረ ብርሃን ፋና ኤፍ ኤም እንደተናገሩት÷ ካለፈው አመት ጀምረው ወደዚህ አሠራር መግባታቸውን ገልጸዋል።
በሄክታር ከ30 እስከ 50 ኩንታል ስንዴ ለማምረት ማቀዳቸውንም ተናግረዋል።
የሰሜን ሸዋ ዞን ግብርና መምሪያ በበኩሉ÷ ከ9 ሺህ 600 ሄክታር በላይ ማሳ ስንዴን በመስኖ በማልማት ከ432 ሺህ 400 ኩንታል በላይ ምርት ለማግኘት መታቀዱን ገልጿል።
በማዳበሪያ እጥረት በኩል የሚነሳውን የአርሶ አደሮች ቅሬታ በፍጥነት ለመፍታትም እየሰራ መሆኑን አስታውቋል።
ከመስኖ ልማት ባሻገር በበጋ ወራት በሚካሄዱ የተፈጥሮ ሃብት ቀጣይ የልማት ስራዎች ላይ ባለድርሻ አካላት በተገኙበት ምክክር ተካሂዷል።
በታለ ማሞ
አካባቢዎን ይጠብቁ!
ወደ ግንባር ይዝመቱ!
መከላከያን ይደግፉ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.