የህዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም የሚያቀርባቸው የእርምት እርምጃዎች እየተተገበሩ አይደለም ተባለ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 9፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም የሚያቀርባቸው የእርምት እርምጃዎች በታችኛውና መካከለኛው የመንግስት አስተዳደር እርከን ተገቢውን ምላሽ እንደማያገኙ ተገለጸ።
ተቋሙ ለሁለት ቀናት የሚቆይ የስድስት ወር የእቅድ አፈፃፀም ሪፖርት ግምገማ በአዳማ ከተማ እያካሄደ ነው።
ተቋሙን እንደገና ለማቋቋም በወጣው አዋጅ ቁጥር 1142/2011 መሰረት የተሰጠውን ስልጣንና ኃላፊነት ስራ ላይ ማዋል እንዲችል ማንኛውም ሰው አስፈላጊውን ድጋፍ የመስጠትና የመተግበር ግዴታ እንዳለበት መደንገጉ ተገልጿል።
ይሁንና በዝቅተኛና መካከለኛው የመንግስት አስተዳደር እርከኖች ላይ ያሉ አስፈጻሚ ተቋማት የቀረቡ የመፍትሄ ሃሳቦችን ከማስፈጸም አንጻር የአመራሮች ቁርጠኝነት ክፍተት እንዳለ ተነስቷል።
በተቋሙ በቀረበ የምርምራ ውጤትና መፍትሄ የእርምት እርምጃዎች ላይ ተባባሪ የማይሆኑ የመንግስት ባለስልጣናት ተጠያቂነት ያለባቸው ሲሆን፥ በ30 ቀናት ውስጥ የእርምት እርምጃ መውሰድ ይገባቸዋልም ተብሏል።
ይህ ሳይሆን ከቀረ ከ5 እስከ 7 ዓመት በሚደርስ እስራት ወይም በ10 ሺህ ብር የገንዘብ ቅጣት ወይም በሁለቱም በገንዘብና በእስራት እንደሚቀጣ በአዋጁ ተቀምጧል።
የሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም ዋና እንባ ጠባቂ ዶክተር እንዳለ ሀይሌ፥ በታችኛውና በመካከለኛው የመንግስት አስተዳደር እርከን ላይ የሚገኙ ተቋማት በቀረቡላቸው የመፍትሄ ሃሳቦች ላይ ተገቢ ምላሽ አለመስጠታቸውን ተናግረዋል።
በመሆኑም በተቋሙ የተሰጡ የመፍትሄ ሃሳቦችን ተግባራዊ ያላደረጉ የመንግስት አስፈጻሚ አካላትን ተጠያቂ ለማድረግ እየተሰራ ነው ብለዋል።
ሃላፊው አያይዘውም ተቋሙ በሀዲያ ዞን ሶሮ ወረዳ አስተዳደርና ጊምቢቹ ከተማ ማዘጋጃ ቤት ሁለት የስራ ሃላፊዎች በዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የወንጀል ክስ መስርቶ እያንዳንዳቸው በ5 ሺህ ብር እንዲቀጡ መደረጋቸውን ጠቁመዋል።
የአዲስ አበባ ቤቶች ልማት አስተዳደር ኤጀንሲ የቀረበለትን የመፍትሄ ሃሳብ ባለመፈፀሙ በአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንዲጋለጥ መደረጉንም ገልጸዋል።
በፌደራል ተቋማት ላይ የህዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም የሚያቀርባቸው የመፍትሄ ሃሳቦችን ተቀብሎ የእርምት እርምጃ ከመውሰድ አንጻር ከጊዜ ወደጊዜ መሻሻል ቢታይም ለጉዳዩ በቂ ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንደሚገባ መገለጹን ኢዜአ ዘግቧል።
ትኩስ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ገፃችንን ሰብስክራይብ ያድርጉ!
https://t.me/fanatelevision