Fana: At a Speed of Life!

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የባሕር ዳር ሀገረ ስብከት እና ደብረብርሃን ዩኒቨርሲቲ ለተፈናቃዮች ድጋፍ አደረጉ

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 20፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የባሕር ዳር ሀገረ ስብከት እና የደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ በአሸባሪው የትህነግ ወራሪ ቡድን ጉዳት የደረሰባቸውን ወገኖች መልሶ ለማቋቋም የሚደረገውን እንቅስቃሴ ለማገዝ ከ5 ሚሊየን ብር በላይ የሚያወጣ የምግብ እና የቁሳቁስ ድጋፍ አደረጉ።
 
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የባሕር ዳር ሀገረ ስብከት ለተፈናቀሉ ወገኖች ማቋቋሚያ 4 ሚሊየን ብር የሚገመት የዓይነት ድጋፍ አድርጋለች፡፡
 
ድጋፉን ያስረከቡት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የባሕር ዳር ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ እና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል አቡነ አብርሃም በመጽሐፈ እያሱ ምዕራፍ 10 ከቁጥር 6 ”ባሪያዎችህን ለመርዳት እጅህን አትመልስ” ተብሎ ተጽፏል፤ ይህንን መሠረት አድርጋ ቅድስት ቤተክርስቲያን መከራውን በመመልከት ድጋፍ ስታደርግ መቆየቷን ገልጸዋል፡፡
 
አሁንም ተፈናቃዮችን መልሶ ለማቋቋም በሚደረገው ሀገራዊ ርብርብ የድርሻዋን ለመወጣት የቻለችውን አድርጋለች፤ ወደፊትም አጠናክራ ትቀጥላለች ነው ያሉት፡፡
 
ድጋፉ በባሕር ዳር ሀገረ ሥብከት ሥር ከሚገኙ ገዳማት እና አብያተክርስቲያናት ሠራተኞች የተውጣጣ ነው ብለዋል፡፡
 
ድጋፉን የተረከቡት የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ድረስ ሳህሉ (ዶክተር) ለተደረገው ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል፡፡
 
ዶክተር ድረስ ድጋፉ በጦርነቱ ለተጎዱ አካባቢዎች ያለው አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑን ነው የተናገሩት፡፡ ቤተክርስቲያኒቱ ቀደም ብላ ከመተከል ዞን ለተፈናቀሉ ወገኖች ድጋፍ ስታደርግ መቆየቷን አስታውሰዋል፡፡
 
በተመሳሳይ የደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ በአሸባሪው የትህነግ ወራሪ ቡድን ጉዳት የደረሰባቸውን ወገኖች መልሶ ለማቋቋም የሚደረገውን እንቅስቃሴ ለማገዝ ከ5 ሚሊየን ብር በላይ የሚያወጣ የምግብ እና የቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ።
 
ድጋፉን ያስረከቡት የደብረብርሃን ዩኒቨርሲቲ አካዳሚ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ደረጀ አንዳርጌ ዩኒቨርሲቲው ለዜጎች ማኅበራዊ አገልግሎት ለመስጠት ከሚያደርገው እንቅስቃሴ በተጨማሪ ከተጎጂዎች ጎን መቆሙን ለመግለጽ ከ5 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ በማድረግ የምግብ እና የቁሳቁስ ድጋፍ ማድረጉን ገልጸዋል።
 
ዩኒቨርሲቲው ቀደም ብሎም በተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ ወገኖችን ለመደገፍ ከ200 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ በማድረግ ድጋፍ ሲያደርግ መቆየቱን ዶክተር ደረጀ ማስታወሳቸውን አሚኮ ዘግቧል።
 
ድጋፉን የተረከቡት የዞኑ ምክትል አስተዳዳሪ እና የትምህርት መምሪያ ሃላፊ ጋሻው አስማሜ ዩኒቨርሲቲው ላደረገው ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።
በዞኑ የደረሰው የተቋማት እና የግለሰቦች የንብረት ውድመት ከፍተኛ በመሆኑ ሌሎች ተቋማትም የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንዲቀጥሉም ጥሪ አቅርበዋል።
 
አካባቢዎን ይጠብቁ!
ወደ ግንባር ይዝመቱ!
መከላከያን ይደግፉ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለ!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.