Fana: At a Speed of Life!

የሚኒስትሮች ምክር ቤት ለ2012 ዓ.ም 27 ነጥብ 89 ቢሊየን ብር ተጨማሪ በጀት አፀደቀ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 9፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የሚኒስትሮች ምክር ቤት የ2012 ዓ.ም በጀት ተጨማሪ 27 ነጥብ 89 ቢሊየን ብር ሆኖ እንዲፀድቅ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መርቷል።

የሚኒስትሮች ምክር ቤት ባሳለፍነው ቅዳሜ ባካሄደው 79ኛው መደበኛ ስብሰባው በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳልፏል።

ምክር ቤቱ በስብሰባው በፌደራል መንግስት ተጨማሪ በጀት እና ወጪ አሸፋፈን ማስተካከያ ረቂቅ አዋጅ ላይ ውይይት አካሂዶ ነው ውሳኔ ያሳለፈው።

በዚህም ተጨማሪ በጀቱ መሰረታዊ መነሻ የሆነው በመንግስት የተዘጋጀ ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ መሆኑ ተጠቁሟል።

በዚህም ዋና አላማው ኢኮኖሚው አሁን ከገጠሙት ተግዳሮቶች የሚላቀቅበት የፖሊሲ እርምጃዎችን ተግባራዊ ለማድረግ 18 ቢሊየን ብር፣ ለልማታዊ ሴፍቲኔት ፕሮግራም ትግበራ 2 ቢሊየን ብር፣ ለእኩል ስራ እኩል ደመወዝ ሀገራዊ ትግበራ 7 ነጥብ 9 ቢሊየን በድምሩ 27 ነጥብ 89 ቢሊየን ተጨማሪ በጀት እንዲፀድቅ የገንዘብ ሚኒስቴር ረቂቅ አዋጅ አዘጋጅቶ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ውሳኔ አቅርቧል።

ምክር ቤቱም በቀረበው ተጨማሪ በጀት ረቂቅ አዋጅ ላይ ተወያይቶ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ ወስኗል።

በመቀጠልም ምክር ቤቱ የተወያየው በገንዘብ ሚኒስቴር የቀረቡትን ለደብረ ማርቆስ ሞጣ የመንገድ ስራ ማሻሻያ ፕሮጀክት፣ ለአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ የልህቀት ማዕከል መመስረቻ ፕሮጀክት እና ለሁለተኛው ሀገር አቀፍ የመጠጥ ውሃ አቅርቦት ሳኒቴሽንና ሃይጅን ፕሮግራም ማስፈጸሚያ የሚውሉ የብድር ስምምነቶች እና ማጽደቂያ ረቂቅ አዋጆች ላይ ነው።

ብድሮቹ ከሀገሪቱ የብድር አስተዳደር ስትራቴጂ ጋር የሚጣጣሙ፣ የ10 ዓመት እፎይታ ያላቸው፣ በረጅም ጊዜ የሚከፈሉ እንዲሁም ወለድ የማይታሰብባቸው በመሆናቸው አዋጆቹ ይፀደቁ ዘንድ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፉ ወስኗል።

ሌላው ምክር ቤቱ የተወያየበት የአፍሪካ ህብረት ሰንደቅ ዓላማ መዝሙርና የአፍሪካ ቀን ረቂቅ አዋጅ ላይ ነው።

ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ሀገራት ጋር ያላት አጋርነት ለማሳደግ፣ ለፓን አፍሪካኒዝም እና ለአፍሪካ የውህደት አጀንዳ ተግባራዊነት ያላትን ቁርጠኝነት ለማስቀጠል እንዲሁም የህብረቱ ኮሚሽን አስተናጋጅ ሀገርነት ሚናዋን ለመወጣት ከምታከናውናቸው ተግባራት በተጨማሪ የአፍሪካ ህብረት ሰንደቅ ዓላምን ማውለብለብ፣ የአፍሪካ ህብረት መዝሙርን ማዘመር እና የአፍሪካ ቀን ታስቦ እንዲውል ማድረጉ ሀገሪቱ ለህብረቱ ዓላማዎች ስኬት ያላትን ቁርጠኝነት የሚያሳይ በመሆኑ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያቀረበውን ረቂቅ አዋጅ እንዲፀድቅ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲላክ መወሰኑን ምክር ቤቱ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት በላከው መግለጫ አስታውቋል።

ምክር ቤቱ ከዚህ ባለፈም የግብርና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ኮሌጆችን ለማቋቋም በተዘጋጀው ረቂቅ ደንብ ላይ በመወያየት ውሳኔ አሳልፏል።

ኮሌጆቹ ተጠሪነታቸው ለግብርና ሚኒስቴር ሆነው ራሳቸውን የቻሉ ህጋዊ ሰውነት ያላቸው ተቋማት እንዲሆኑ እና በግብርናው ዘርፍ በሀገሪቱ ልዩ ፍላጎቶች ላይ አተኩረው እንዲሰሩ ማድረግ እንዲቻል ሚኒስቴሩ ረቂቅ ደንቡን ማዘጋጀቱ ተጠቁሟል።

የሚኒስትሮች ምክር ቤትም በቀረበው ረቂቅ ደንብ ላይ ከተወያየ በኋላ አንዳንድ ማስተካከያዎችን በመጨመር ደንቡ በነጋሪት ጋዜጣ እንዲወጣ እና በስራ ላይ እንዲውል ውሳኔ አሳልፏል።

ትኩስ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ገፃችንን ሰብስክራይብ ያድርጉ!
https://t.me/fanatelevision

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.