Fana: At a Speed of Life!

በእውቀት የታነፀ፤ መሠረቱን በሠላም ላይ የሚጥል ትውልድ ማፍራት ይገባል-የሃይማኖት አባቶች

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 23፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያን አንድነትና ቀጣይነት ለማረጋገጥ በእውቀት የታነፀ እና መሰረቱን በሠላም ላይ የሚጥል ትውልድ ማፍራት እንደሚገባ የሃይማኖት አባቶች አሳሰቡ፡፡
 
በአሸባሪው ህወሓት የወደመውን የወልድያ ዩኒቨርሲቲ የጎበኙት የሃይማኖት አባቶቹ ውድመቱን ‘ኢትዮጵያዊ ስነ-ልቦና ያለው አካል አደረገው ለማለት አያስደፍርም’ ብለዋል፡፡
 
ሆኖም አሸባሪው ቡድን ከኢትዮጵያዊነት ስነ ምግባር ያፈነገጠ፣ የትውልዱ የወደፊት ዕጣ ፈንታ የማያሳስበው አረመኔ መሆኑን ያሳየበት ነው ብለውታል።
 
የፈጸመው ድርጊት ትናንት በድብቅ በሰው አዕምሮ ላይ ሲሰራ የነበረውን ውድመት ዛሬ በንብረት ላይ ይፋ ማውጣቱን ነው የገለጹት፡፡
 
ይህን ለማስተካከል የሃይማኖት አባቶችና መንግስት ተቀናጅተው በዕውቀት የታነጸ እና በሠላም ላይ መሰረቱን የሚጥል ትውልድ ማፍራት እንደሚጠበቅባቸው አስገንዝበዋል።
 
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስቲያን የባህር ዳር አገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ አብርሃም በወልድያ ዩኒቨርሲቲ ላይ አሳዛኝ ውድመት መድረሱን መመልከታቸውን ተናግረዋል፡፡
 
ይህን ውድመት ኢትዮጵያዊያን አደረጉት ለማለት እንኳ የሚያስደፍር አይደለም ያሉት አቡነ አብርሃም ትምህርት ቤት የሁሉም የእውቀት ማዕከል እንጂ የአንድ ድርጅት ወይም የመንግስት አይደለም ብለዋል።
 
ከኢትዮጵያ በተጨማሪ የውጭ አገራት ተማሪዎችን ተቀብሎ በሚያስተምረው ወልድያ ዩኒቨርሲቲ ላይ ይህ ድርጊት በመፈጸሙ በእጅጉ ማዘናቸውን ገልፀዋል፡፡
 
የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተ-ክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ ካርዲናል ብርሃነ ኢየሱስ በበኩላቸው በወልድያ ዩኒቨርሲቲ ባዩት ውድመት ማዘናቸውን ተናግረዋል፡፡
 
መጽሃፍቶች ተቀዳደው፣ የኢንጂነሪንግ እና የፊዚክስ ላቦራቶሪዎች ወድመው ተመልክተናል ያሉት ካርዲናል ብርሃነ ኢየሱስ ይህ እጅግ የሚያሳዝን፤ የሃይማኖት አባቶችም የሚያወግዙት ተግባር መሆኑን ነው የገለጹት።
 
በየትኛውም ዓለም በጦርነት ከማይደፈሩ ተቋማት መካከል የትምህርት እና የጤና ተቋማት ይገኙበታል ያሉት ደግሞ የኢትዮጵያ ወንጌላዊያን ኅብረት ፕሬዚዳንት ፓስተር ጻድቁ አብዶ ናቸው፡፡
 
አሸባሪው የህወሓት ቡድን ግን ይህን ወደጎን በመተው ከተሞች ውስጥ ጦርነት ባልተካሄደበት ሁኔታ ሆን ብሎ እነዚህን ተቋማት እንዳወደመ መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
 
የሃይማኖት አባቶቹ የወደሙ ተቋማትን ከቀድሞው በተሻለ መልኩ መገንባት የሁሉም ኢትዮጵያዊያን ሃላፊነት በመሆኑ በአንድነት መቆም እንደሚገባም አስገንዝበዋል፡፡
 
የወደመው ተጠግኖ በእውቀት የታነጸ፣ በሠላም ላይ መሰረቱን የሚጥል ትውልድ ለማፍራት ሁላችንም ደፋ ቀና ማለት አለብን ሲሉም አባቶቹ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
 
ወገኑን የሚያከብርና አገሩን እንደ ጥንት አባቶች የሚወድ ትውልድ ለማፍራት የሃይማኖት አባቶችን ጨምሮ ሁሉም ሃላፊነታቸውን እንዲወጡም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.