Fana: At a Speed of Life!

ለመንግስት ሠራተኞች የብቃት ማረጋገጫ ፈተና ሊሰጥ ነው

አዲስ አበባ፣ የካቲት 9፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) ከመጭው ሚያዝያ ወር ጀምሮ በመንግስታዊ መዋቅር ውስጥ ለሚገኙ ሠራተኞች የብቃት ማረጋገጫ ፈተና እንደሚሰጥ የሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን አስታወቀ።

የሲቪል ሰርቪስ ብቃት ማረጋገጫ ማዕቀፍ ፕሮጀክት መጀመርን አስመልክቶ ግንዛቤ ለማስጨበጥ የተዘጋጀ የምክክር መድረክ በአዳማ ከተማ እየተካሄደ ነው።

የኮሚሽኑ ምክትል ኮሚሽነር አቶ ብርሃኑ ፈይሳ እንደገለጹት÷ የብቃት ማረጋገጫ ፈተናው የሚሰጠው ከሀገራዊ ለውጡ ጋር የተቃኘ የመንግስት ሰራተኛ እንዲኖርና የወቅቱን የህዝብ ጥያቄ የሚመልስ ኃይል ለመፍጠር በሚያስችል መልኩ ነው።

በአሁኑ ወቅት የህብረሰተቡን የአገልግሎት ፍላጎት ማርካት እንዳልተቻለ ጠቅሰው ለዚህ ምላሽ እንዲሆንም በመንግስታዊ መዋቅር ውስጥ ያለው ማንኛውም ሠራተኛ በዚህ የብቃት ማረጋገጫ ውስጥ እንደሚያልፍ ተናግረዋል።

የብቃት ማረጋጫ ፕሮጀክቱ ለሁለት ዓመት ተኩል የሚቆይ ነው ያሉት ምክትል ኮሚሽነሩ፥ ከመጭው ሚያዝያ ወር ጀምሮ ወደ ተቋማቱ አዲስ የሚቀላቀሉ ሠራተኞችም ጭምር የብቃት ማረጋገጫ ፈተና እንደሚወስዱ ገልጸዋል።

በሀገሪቱ ከ1 ሚሊየን 700 ሺህ በላይ የመንግስት ሰራተኞች እንደሚኖሩ ያመለከቱት አቶ ብርሃኑ፥ ፕሮጀክቱ በዘርፉ መሰረታዊ ለውጥ ያመጣል ተብሎ የታመነበትና በጠቅላይ ሚኒስትሩ ተቀባይነት ያገኘ መሆኑንም አስረድተዋል።

በኮሚሽኑ የብቃት ማረጋገጫ ፕሮጀክት ሥራ አስኪያጅ አቶ የማነ ኃይሉ በበኩላቸው፥ የፕሮጀክቱ ዓላማ የመንግስት አገልግሎት አሰጣጥን ውጤታማ ለማድረግና የህዝቡን የተገልጋይነት እርካታ ለማረጋገጥ ነው ብለዋል።

ሀገሪቱ የቆየና ዘመን ተሻጋሪ መንግስታዊ የሲቪል ሰርቪስ አደረጃጀት ቢኖራትም በተለይም ከአቅም፣ አመለካከት፣ አስተሳሰብና ተግባቦት አንጻር ሰፊ ክፍተት እንዳለ አንስተዋል።

ፕሮጀክቱ የተቀረጸው ሀገሪቱ የደረሰችበትን ደረጃ የሚመጥንና ከለውጡ ጋር የታቀኘ አስተሳሰብና ተግባር ያነገበ እውቀት፣ ክህሎትና በአመለካከት የበቃ የሰው ኃይል በአዲስ መልክ ማደራጀት በማስፈለጉ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

የብቃት ማረጋገጫ ፈተናው የየሴክተሮቹን ዓላማ መሰረት ባደረገ መልኩ በሠራተኞች እውቀትና ክህሎት ላይ በመመስረት በሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ ሥር ሆኖ ከፌደራል እስከ ክልል ድረስ እንደሚሰጥ አስታውቀዋል።

ከዛሬ ጀምሮ ለሁለት ቀናት በሚቆየው የምክክር መድረኩ ከፌዴራል፣ ከክልሎችና ሁለቱ የከተማ አስተዳደሮች እንዲሁም ከዩኒቨርሲቲዎችና ኮሌጆች የተውጣጡ የዘርፉ አመራሮችና ባለሙያዎች እየተሳተፉ መሆኑን ኢዜአ ዘግቧል።

ትኩስ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ገፃችንን ሰብስክራይብ ያድርጉ!
https://t.me/fanatelevision

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.