የአፍሪካ ልማት ባንክ ከአዲስ አበባ ሱዳን ለሚዘረጋው የባቡር ሃዲድ የንድፍ ስራ ድጋፍ ሊያደርግ ነው
አዲስ አበባ፣ የካቲት 9፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የአፍሪካ ልማት ባንክ ከአዲስ አበባ ሱዳን የሚያገናኘውን የባቡር ሃዲድ መስመር ዝርጋታ ዲዛይን ስራ ለመደገፍ የሚያስችል ዝግጅት ማጠናቀቁን አስታወቀ።
የአፍሪካ ልማት ባንክ ፕሬዚዳንት ዶክተር አኪንውሚ አዴሴና ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ባደረጉት ቆይታ፥ ባንኩ በኢትዮጵያ በርካታ የልማት ስራዎችን እየደገፈ መሆኑን አብራርተዋል።
በባንኩ ድጋፍ እየተገነባ ያለው የአዲስ አበባ ናይሮቢ መንገድም የሁለቱን ሀገራት የንግድ ልውውጥ በከፍተኛ ደረጃ ያሳድገዋል የሚል እምነት እንዳላቸውም ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ የተሻለ ውጤት እያስመዘገበችበት ያለውን የጤና ዘርፍ እና የስነ ምግብ ጉዳይ ባንኩ እየደገፈ መሆኑንም ነው የተናገሩት።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ አስተዳደር ተስፈኛ ነን ያሉት የባንኩ ፕሬዚዳንት በተለይ የኢትዮጵያ የምጣኔ ሀብት የጀርባ አጥንት የሆነውን የግብርና ምርታማነት ለማሳደግ በሚደረገው እንቅስቃሴ ድጋፋችን ተጠናክሮ ይቀጥላል ነው ያሉት።
ዶክተር አዴሴና ከግብርናው ዘርፍ ባለፈም በምስራቅ አፍሪካ ለማምጣት የታሰበውን የምጣኔ ሀብት ውህደት ለማፋጠን ኢትዮጵያ የጀመረቻቸውን የልማት ስራዎች ባንኩ እየደገፈ መሆኑን ገልፀዋል።
ፕሬዚዳንቱ የአፍሪካ መንግስታት አህጉሪቷ ተስፋ የጣለችበትን አጀንዳ 2063 ለማሳካት የጀመሩትን እንቅስቃሴ ማጠናከር እንዳለባቸውም ገልጸዋል።
አባል ሀገራቱ እንደ ኢትዮጵያ በ50 ዓመታት የሚተገበረውን አጀንዳ ከብሄራዊ የልማት ግቦቻቸው ጋር አቀናጅተው መተግበር ይኖርባቸዋልም ብለዋል።
አህጉራዊው ባንክ የ2063 የልማት ግቦችን እውን ለማድረግ የሚያስችለውን ስትራቴጂ መቅረፁንም አስታውቀዋል።
በስላባት ማናዬ
ትኩስ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ገፃችንን ሰብስክራይብ ያድርጉ!
https://t.me/fanatelevision