Fana: At a Speed of Life!

አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በአማራ እና አፋር ክልሎች የደረሱ ሰብዓዊና ቁሳዊ ውድመቶችን ሊያጠና ነው

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 25፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የጥናትና የምርምር ቡድን በማቋቋም የሽብር ቡድኑ በአማራና በአፋር ክልሎች ያደረሳቸው ሰብዓዊ ጥሰቶችንና የንብረት ውድመቶችን እንደሚያጠና አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አስታወቀ።
የተለያዩ ተመራቂ ተማሪዎችም የደረሱ ሰብዓዊና ቁሳዊ ውድመቶችን እንዲያጠኑ ድጋፍ እንደሚደረግም ገልጿል።
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ጣሰው ወልደ ሃና ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደተናገሩት፣ በአገራችን ጦርነት በነበረባቸው የአማራና አፋር ክልሎችና በአንዳንድ አካባቢዎች የደረሰውን የሕይወትና የንብረት ውድመት በመስክ የሚያጠና ግብረ-ኃይል ተቋቁሞ የጥናትና የምርምር ስራ ጀምሯል።
ከጥናትና ምርምር ቡድኑ የሚገኘው የጥናት ግኝት መሠረት በማድረግም ውድመቱን ያደረሰውን አሸባሪ ቡድን የታሪክ ተወቃሽ ለማድረግና በቀጣይ ለሚኖሩ የጥናትና ምርምር ስራዎች ይውላል ብለዋል።
አሸባሪ ቡድኑ የፈጸማቸው ሰብዓዊና ቁሳዊ ውድመቶች እጅግ ዘግናኝና የሰው ልጅ በወገኑ ላይ ይፈጽማቸዋል ተብሎ እንደማይታሰብ የገለጹት ፕሬዚዳንቱ የደረሱትን ውድመቶች በሙሉ በተደራጀ መልኩ በማጥናትም መጪው ትውልድ የሽብር ቡድኑን አረመኔነት እንዲገነዘብና ኢትዮጵያም ያለፈችበትን የታሪክ ውጣውረድ ሰንዶ ለማስቀመጥ ይረዳል ብለዋል።
አሁን ላይ በእውነተኛ የጥናት መረጃ ተመሥርተን መረጃዎችን ካልዘገብንና ካላስቀመጥን የኢትዮጵያን ታሪክ ማበላሸት ነው ያሉት ፕሬዚዳንቱ፣ ቡድኑ በመስክ በማጥናት ታሪክ እንዳይበላሽ መረጃዎችን አጥርቶ ያጠናልም ብለዋል።
ከጥናትና ምርምሩ ጎን ለጎንም በአሸባሪው ቡድን ከፍተኛ ውድመት የደረሰባቸውን የወልዲያ ዩኒቨርሲቲ፣ መካነ-ሰላም ዩኒቨርሲቲ፣ ወሎ ዩኒቨርሲቲና ሌሎቹንም ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትን መልሶ ለማቋቋም በመስራት እንደሚገኝ ጠቅሰዋል።
በአሸባሪ ቡድኑ የወደሙ ዩኒቨርሲቲዎችን መልሶ ለማቋቋምም ዩኒቨርሲቲው ግብረ- ኃይል አቋቁሞ ተግባራዊ እንቅስቃሴ መጀመሩንም ፕሬዚዳንቱ ተናግረዋል ሲል ኢፕድ ዘግቧል።
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.