Fana: At a Speed of Life!

ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን እጩ ኮሚሽነሮች አቀራረብ ስርዓት ተዘረጋ

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 25፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ አገራዊ የምክክር ኮሚሽን እጩ ኮሚሽነሮች አቀራረብ ስርዓት በኢፌዲሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መዘርጋቱን አፈ-ጉባኤ ታገሰ ጫፎ ተናገሩ፡፡
 
በዚህ መሰረትም በየእጩ ኮሚሽነሮችን ጥቆማ የሚቀበልና የሚያደራጅ የጥቆማ ተቀባይ ኮሚቴ የተቋቋመ ሲሆን፥ የእጩ ኮሚሽነሮችን ጥቆማ ከመቀበል ጀምሮ በምክር ቤቱ ቀርበው እስከሚሾሙበት ድረስ የተለያዩ ተግባራትን እንደሚያከናውን ተመላክቷል፡፡
 
ለዚህም የጽህፈት ቤቱ ሰብሳቢ ዶክተር ሄኖክ ስዩም እና ሌሎች ሁለት አባላት መካተታቸውን ነው አፈ ጉባኤው የገለጹት፡፡
 
የምክክር ኮሚሽኑን እጩ ኮሚሽነሮች ጥቆማ አቀባበል አሳታፊ፣ ግልጽ፣ ታዓማኒና ከአድሎ የጸዳ እንዲሆን ለማስቻል የሚያግዝ የአማካሪ ቡድንም ተቋቁሟል ነው ያሉት፡፡

 

አማካሪ ቡድኑ በምክር ቤቱ አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ የሚመራ ሲሆን÷ የፌዴሬሽን ምክርቤት አፈ ጉባኤ፣ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት እንዲሁም የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ እና  የሲቪክ ማህበራት ጥምረት ተወካዮች በአባልነት ተካተውበታል፡፡

ቡድኑ የተለያዩ ተግባራት እና ኃላፊነቶች የተሰጡት መሆኑን የጠቀሱት አፈ ጉባኤው÷ ከቀረቡ እጩዎች ውስጥ በአዋጁ ላይ የተቀመጡትን መስፈርቶች በከፍተኛ ደረጃ የሚያሟሉትን እጩዎች በመለየት ረገድ አፈ ጉባኤውን ማማከር ዋነኛው ስለመሆኑ ዛሬ በተደረገው ውይይት ላይ ጠቁመዋል፡፡

የጥቆማ መስጫ መርሃ ግብርና ጥቆማ የሚሰጥበት ፎርማት ገና ይፋ ሳይደረግ ጥቆማዎች እየቀረቡ ስለመሆኑ አፈ ጉባኤው ገልጸው÷ እነዚህ ጥቆማዎችም ተቀባይነት እንደማይኖራቸው ማስገንዘባቸውን ከምክር ቤቱ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን እጩ ኮሚሽነሮች ማቅረቢያ ጊዜ፣  ፎርማትና አጠቃላይ የእጩዎች አቀራረብ ስርዓትን በተመለከተ አፈጉባኤው ዛሬ ከሰዓት በኋላ ጋዜጣዊ መግለጫ እንደሚሰጡ ይጠበቃል፡፡

 
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
 
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.