የሀገር ውስጥ ዜና

የኅብረ ብሔራዊ ዘመቻ ድል ባለቤት ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን ናቸው -ሽመልስ አብዲሳ

By Alemayehu Geremew

January 03, 2022

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 25፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) “ድል ለሁሉም” በሚል መሪ ቃል ላለፉት ሦስት ቀናት በአዳማ ከተማ ሲካሄድ የቆየው የአመራሮች ውይይት ተጠናቀቀ፡፡

በውይይቱ የአንድነትና የኅብረ ብሔራዊነት ዘመቻ ድል ባለቤት ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን መሆናቸውን የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ ገልጸዋል፡፡

የአመራሮቹ ውይይት በኅብረ ብሔራዊ ዘመቻው የተገኙ ድሎች፣ የታዩ ክፍተቶች እና ቀጣይ አቅጣጫዎች ላይ ያተኮረ ነው።

ከአሸባሪውና ወራሪው ቡድን መደምሰስ በኋላ የተደረገው ይህ ውይይት ለሌላ ድል ራስን ለማዘጋጀት እና ሰላምን ለማረጋገጥ አስቻይ ምህዳር እንደሚፈጥርም ተመላክቷል፡፡

በቀጣይም ተጨባጭ ስልቶችን ቀይሶ ሀገርን ለማስቀጠል ጠንክሮ መሥራት እንደሚገባ ከመድረኩ ተነስቶ ስምምነት ላይ መደረሱ ተገልጿል፡፡

የውጪ እና የውስጥ ጠላቶች ግንባር ፈጥረው ያቀናበሩትን ሴራ በጠንካራ አመራርና የህዝብ አንድነት ማክሸፍ ተችሏልም ነው የተባለው፡፡

ከውይይቱ በኋላ የተፈጠሩ መልካም እድሎችና መስተካከል ያለባቸውን ጉዳዮች ቆጥሮ በመረከብ ተግባራዊ በማድረግ መግባባት ላይ ተደርሷል፡፡

የኦሮሚያ ብልጽግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ፍቃዱ ተሰማ ÷ ውይይቱ በወቅታዊ ሁኔታ ላይ ያተኮረ እናየጋራ አቀም ላይ የተደረሰበት መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

በውይይቱ ላይ ኢትዮጵያውያን በሀገር ጉዳይ ላይ በጋራ የቆሙ የቁርጥ ቀን ልጆች መሆናቸውን አስመስክረዋልም ብለዋል ሃላፊው፡፡

ከነገ ጀምሮ ውይይቱ በክልሉ ዞኖች እና ከተሞች ደረጃ ወርዶ ተመሳሳይ ውይይት እንደሚደሚካሄድ ከኦሮሚያ ብልጽግና ፓርቲ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡