Fana: At a Speed of Life!

የገበያ ዋጋ ለማረጋጋት ከፍተኛ መጠን ያለው የስንዴና ዘይት ግዢ ተፈጸመ

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 26፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የተረጋጋ ማክሮ ኢኮኖሚ ከማስፍን አንጻር የዋጋ ግሽበትን የመቆጣጠርና የገበያ ዋጋን የማረጋጋት ፋይዳ ያለው የ4 ሚሊየን ኩንታል ስንዴና የ12 ነጥብ 5 ሚሊየን ሊትር የምግብ ዘይት ግዢ መፈጸሙ ተገለጸ፡፡

የገንዘብ ሚኒስቴርና የተጠሪ ተቋማት የመቶ ቀን እቅድ አፈጻጸም ግምገማ በተካሄደበት ወቅት እንደተገጸው ባለፉት ጥቅምትና ህዳር ወራት የ4 ሚሊየን ኩንታል ስንዴ ግዥ የተከናወነ ሲሆን ÷ ከዚህ ውስጥ 1 ሚሊየን 51 ሺህ 160 ኩንታል ስንዴ ወደ አገር ውስጥ መግባቱ ተገልጿል፡፡

ይህም የስንዴ ዋጋ ከፍ እንዳይል የራሱ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ታምኖበታል፡፡

የተቀረውም ስንዴ በተቻለ ፍጥነት ተጓጉዞ ወደ አገር ውስጥ አንደሚገባም ታወቋል፡፡

በዚሁ ወቅት የ12 ነጥብ 5 ሚሊየን ሊትር የምግብ ዘይት ግዢ ተፈጽሞ ወደ አገር ውስጥ ለማስገባት በሂደት ላይ መሆኑም ተመልክቷል፡፡

ከዚሁ ጋር በተያያዘም የምግብ ዘይትና ዱቄት ከውጭ በፍራንኮ ቫሉታ (አስመጪዎች በራሳቸው የውጭ ምንዛሪ) እንዲያስገቡ በመደረጉ የሸቀጦች ዋጋ ባለበት እንዲቀጥል ማስቻሉም ተገልጿል፡፡

በመሆኑም በጥቅምት ወር 2014 ዓ.ም 34 ነጥብ 2 በመቶ የነበረ አጠቃላይ የዋጋ ግሽበት በህዳር ወር ወደ 33 በመቶ ዝቅ ብሏል፡፡

የሕዳር 2014 ወርሃዊ የምግብ ዋጋ ግሽበት ካለፈው ጥቅምት 2014 ጋር ሲነጻጸር በ1 ነጥብ 8 በመቶ የቀነሰ ሲሆን÷ በተመሳሳይ ጊዜ ውስጥ ምግብ ነክ ያልሆኑ ሸቀጦች የዋጋ ግሽበት 1 ከመቶ የጨመረ መሆኑን ከገንዘብ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያሳያል፡፡

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.