የሀገር ውስጥ ዜና

መቄዶኒያ የአረጋውያንና የአዕምሮ ህሙማን መርጃ ማዕከል ከ20 ሚሊየን ብር በላይ ድጋፍ አደረገ

By Alemayehu Geremew

January 04, 2022

መቄዶኒያ የአረጋውያንና የአዕምሮ ህሙማን መርጃ ማዕከል ከ20 ሚሊየን ብር በላይ ድጋፍ አደረገ

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 26 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) መቄዶኒያ የአረጋውያንና የአዕምሮ ህሙማን መርጃ ማዕከል በሽብር ቡድኑ ህወሃት ጥቃት ደርሶባቸው ለተፈናቀሉ ወገኖች ከ20 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመት የዓይነት ድጋፍ መላኩ ተገለጸ።

ከሰባት ሺህ አምስት መቶ በላይ ጧሪ ደጋፊ የሌላቸው ወገኖችን እየረዳ የሚገኘው የመቄዶኒያ ማዕከል በሽብር ቡድኑ ወረራ የተፈናቀሉ ወገኖችን በቋሚነት ለመርዳት ማቀዱን ገልጿል።

በአማራ ክልል ከዋግኸምራ አካባቢ ለተፈናቀሉ ወገኖች የሚውል የዓይነት ድጋፍ በ10 ከባድ ተሽከርካሪዎች ተጭኖ ወደ ስፍራው ተጉዟል።

የመቄዶኒያ ማዕከል ከዚህ ቀደም በሽብር ቡድኑ ወረራ ምክንያት ለተፈናቀሉና ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች ከሰኔ ወር ጀምሮ በሸዋ ሮቢት፣ ደሴ፣ አጣዬ፣ ኩታበር፣ ጋይንት እና ሌሎች አካባቢዎችም በተደጋጋሚ ድጋፍ ሲያደርግ መቆየቱ ተገልጿል።

ወደ ዋግኸምራ ከተላከው ድጋፍ ውስጥ አልባሳት፣ ምግብ ነክ የሆኑ ፓስታ፣ መኮረኒ ፣ ድርቆሽ፣ የስንዴ ዱቄት እና የህጻናት አልሚ ምግቦች ይገኙበታል።

“የተቸገሩ ወገኖችን ለመርዳት ሀብታም መሆን አይጠይቅም’፤ ድጋፍ ለማድረግም የተረፈን ሊሆን አይገባም” ያሉት የማዕከሉ መስራችና ስራ አስኪያጅ አቶ ቢኒያም በለጠ÷ የማዕከሉ ተረጂዎች ከቁርሳቸው ቀንሰው አጋርነታቸውን አሳይተዋል ብለዋል።

የመቄዶኒያ ማዕከል ከ7 ሺህ በላይ የአዕምሮ ህሙማንና አረጋውያንን እየረዳ፥ ካለው ላይ ቀንሶ ሲሰጥ ሌላውም ከዚህ ብዙ ሊማር ይገባል ነው ያሉት።

ድጋፉ በቀጣይ በሌሎች የአማራ እና አፋር ክልሎች አካባቢ እንደሚቀጥል እና ኅብረተሰቡ ለመቄዶኒያ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባው ጥሪ አቅርበዋል።

በሃይማኖት ኢያሱ