Fana: At a Speed of Life!

በላልይበላ የገና በዓልን በድምቀት ለማክበር የሚያስችል የመሠረተ ልማት ዝርጋታ መጠናቀቁ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 26 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በታሪካዊቷ የላልይበላ ከተማ የገና በዓልን ባሕላዊና ሃይማኖታዊ ይዘቱን ጠብቆ በድምቀት ለማክበር የሚያስችል የመሰረተ ልማት ዝርጋታ መጠናቀቁን የአማራ ክልል ቱሪዝም ቢሮ አስታወቀ።

የቢሮው ምክትል ሃላፊ ኤርሚያስ መኮንን እንደገለጹት ÷ የላልይበላ ከተማ ለረጅም ጊዜ በአሸባሪው ህወሓት ወረራ ስር በመቆየቷ መጠነ ሰፊ የመሰረተ ልማት ውደመት አድርሶባታል።

አሁን ላይ በከተማዋ የወደሙ የውሃ፣ የቴሌኮም፣ የመብራትና ሌሎች የመሰረተ ልማቶች ተጠግነውና ተሟልተው ለአገልግሎት መብቃታቸውንም ነው የተናገሩት።

የመሠረተ ልማቶቹ አገልግሎት መጀመር ፣ ሆቴሎችና ሌሎች የህዝብ አገልግሎት መስጫ ተቋማት ሥራ ጀምረው ለበዓሉ የሚመጡ እንግዶችን በኢትዮጵያዊ የእንግዳ አቀባበል ለማስተናገድ ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥርላቸው ነው ሃላፊው ያመላከቱት።

የኢንተርኔትና የስልክ አገልግሎቶች ክፍት በመደረጋቸውም የአገር ውስጥና የውጭ ጎብኚዎች ከዓለም አቀፉም ሆነ ከአገር ውስጥ ማህበረሰብ ጋር የሚኖራቸውን ግንኙነት የተሳለጠ እንደሚያደርገው ነው የገለጹት።

በአሁን ወቅት የአገር ውስጥና የውጭ ጎብኝዋች የገና በዓልን ለማክበር ወደ ከተማዋ እየገቡ መሆናቸውንም አመልክተዋል።

የፌደራልና የክልል ተቋማት በከተማዋ የመሰረተ ልማት የማሟላት ስራቸውን በተሳካ ሁኔታ በማጠናቀቅ የበኩላቸውን ድርሻ በመወጣታቸው ምስጋና አቅርበዋል።

በቀጣይም ጥምቀትን በጎንደር፣ የግዮን በዓልን በሰከላና ረጅም ዘመን ያስቆጠረው የአገው ፈረሰኞች ማህበር በዓልን በእንጅባራ ከተማ በድምቀት ለማክበር ዝግጅት እየተደረገ በመሆኑ እንግዶች እንዲታደሙ ጥሪ ማስተላለፋቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.