ጨፌ ኦሮሚያ መደበኛ ጉባኤውን ማካሄድ ጀመረ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 10፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) ጨፌ ኦሮሚያ መደበኛ ጉባኤውን በዛሬው እለት ማካሄድ ጀምሯል።
ጉባዔውን በንግግር የከፈቱት የጨፌ ኦሮሚያ አፈ ጉባዔ ወይዘሮ ሎሚ በዶ፥ ጨፌው የ2012 እቅድ እና በጀት አጽድቆ ወደ ስራ ከገባ በኋላ በክልሉ የተከናወኑ የልማት እና የመልካም አስተዳደር ስራዎች ምን ደረጃ ላይ እንደሚገኙ በቋሚ ኮሚቴዎች ሲገመገም እንደነበር አንስተዋል።
አፈ ጉባዔዋ ወይዘሮ ሎሚ በማከልም፥ ክልሉን የአመጽ ማእከል ለማድረግ አቅደው የሚሰሩ ሀይሎች መንግስት ሰላምን ለማስፈን የሚሰራቸው ስራዎች እንዳይሳኩ በማድረግ በምእራብ እና ደቡብ ኦሮሚያ ዞኖች የሚገኙ ህዝቦች ለፀጥታ ችግር መጋለጣቸውን አንስተዋል።
ዘመኑ አሸናፊ የሆነ ሀሳብ በመያዝ ህዝቡን ከጎን በማሰለፍ ጥያቄዎቹን ለመመለስ የምንነሳበት ወቅት እንጂ በጦር መሳሪያ ፍላጎት የሚሳካበት እንዳልሆነ መገንዘብ ይገባል ብለዋል።
ሰላምን በማረጋገጥ ውስጥ የህዝቡ ሚና ከፍተኛና ወሳኝ በመሆኑ ህዝቡ እንደ ከዚህ ቀደሙ ሁሉ የህግ የበላይነትን በማስከበር ውስጥ የበኩሉን ሚና እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል።
በ2012 ዓ.ም መጨረሻ ላይ ሀገር አቀፍ እና ክልላዊ ምርጫ እንደሚካሄድ በመጥቀስ፤ ምርጫው ዴሞክራሲያዊ፣ ፍትሃዊ እና ነፃ እንዲሆን፣ የፖለቲካ ፓርቲዎችም ፕሮግራማቸውን ለህዝቡ እንዲያስተዋውቁ እንዲሁም ህዝቡም ይበጀኛል ያለውን ፓርቲ መምረጥ እንዲችል በቀጣይ ወራት ሰላምን የማረጋገጥ ስራ የመንግስት ቀዳሚ እና ዋነኛ ስራ መሆን እንደሚገባው አሳስበዋል።
የኦሮሚያ ክልል ምክትል ርእሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳም የመንግስትን የስድስት ወራት የስራ አፈፃፀም ሪፖርት ያቀረቡ ሲሆን፥ በዚህም የክልሉ መንግስት የህዝቡን ፍላጎት፣ መብት እና ጥቅም በማስከበር፣ የህግ የበላይነትን በማረጋገጥ፣ ከአዋሳኝ ክልሎች ጋር ያለውን ግንኙነት በማጠናከር ወደ ብልፅግና ለማሸጋገር በትኩረት እየሰራ መቆየቱን ገልፀዋል።
ከግብርና ልማት ጋር ተያይዞም ግብርና ለኢንዱስትሪ ልማት መሰረት መሆኑን በመግለፅ ክልሉ በቡና ልማት ዘርፍ ያለውን አቅም ለማሳደግ 147 ሚሊየን ብር በመመደብ በአፈር አሲዳማነት ለተጎዱ 10 ዞኖች እና 75 ወረዳዎች የቡና፣ ሻይ እና አቮካዶ ልማት መከናወኑን ተናግረዋል።
እንዲሁም ለውጭ ገበያ በሚቀርቡ የጥራጥሬ እና የቅባት እህሎች ልማት ላይም ትኩረት ተሰጥቶ ሲሰራ መቆየቱን አስታውቀዋል።
ለግብርና ሜካናይዜሽን ብድር የሚውል የ4 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር ብድር መቅረቡን ያነሱት ምክትል ርእሰ መስተዳደሩ፥ 350 ትራክተሮችን ወደ ሀገር ውስጥ በማስገባት በአነስተኛና ጥቃቅን ለተደራጁ 142 ማህበራት በብድር መሰጠቱን ጠቁመዋል።
ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ ባለፈው ክረምት ከተተከሉ 1 ነጥብ 9 ቢሊየን ችግኞች ውስጥ 1 ነጥብ 6 ቢሊየኑ ክብካቤ እየተደረገላቸው እንደሚገኝም አስታውቀዋል።
በመንገድ ልማት ዘርፍም 203 ነጥብ 7 ኪሎ ሜትር የጠጠር ማልበስ ስራ መሰራቱን፣ 218 ነጥብ 6 ኪሎ ሜትር መንገድ ስራ ተጠናቆ ለአገልግሎት ክፍት መደረጉን እና 3 ሺህ 144 ኪሎ ሜትር መንገድ ጥገና መካሄዱን ገልፀዋል።
ከመሬት አስተዳደር ጋር ተያይዞ ዘመናዊ የሆነ የመሬት አስተዳደር ስርዓት የመዘርጋት እና ህገ ወጥ የመሬት ወረራን የመከላከል ስራዎች መሰራታቸውንም አስታውቅዋል።
ከንፁህ መጠጥ ውሃ ጋር ተያይዞም በ2011 በጀት ዓመት መጨረሻ ላይ 66 በመቶ የነበረውን የክልሉን የንፁህ መጠጥ ውሃ ተደራሽነት በ2012 በጀት ዓመት ስድስት ወራት ወደ 74 በመቶ በማሳደግ ተጨማሪ 2 ነጥብ 6 ሚሊየን ሰዎችን የንፁህ መጠጥ ውሃ ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉንም አስታውቅዋል።
በስራ እድል ፈጠራም ባለፉት ስድስት ወራት ከ365 ሺህ በላይ ሰዎች በቋሚነት፣ ከ174 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ሰዎች ደግሞ በጊዜያዊነት፤ በአጠቃላይ ከ540 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ሰዎች የስራ እድል ተፈጥሯል፤ ይህም ከተያዘው እቅድ አንፃር ሲታይም 98 በመቶ ማሳካት እንደተቻለ ነው አቶ ሽመልስ ያስታወቁት።
ከገቢ ጋር ተያይዞም ባለፉት ስድስት ወራት 11 ነጥብ 53 ቢሊየን ብር ለመሰብሰብ ታቅዶ 11 ነጥብ 89 ቢሊየን ብር መሰብሰብ ተችሏል ያሉ ሲሆን፥ ይህም ከተያዘው እቅድ 104 በመቶ ማሳካት ተችሏል ነው ያሉት።
በአጠቃላይ ያለፉት ስድስት ወራት እቅድ አፈፃፀም ሲገመገም፤ ያለው እቅድ እና የስራ አፈፃፀም ከሴክተር ሴክተር የሚለያይ መሆኑና ሁሉም ስራ ተጠናቆ ባይሰራም፤ ዋና ዋና ጉዳዮች መከናወናቸው ተስፋ የሚሰጥ ነው ያሉት አቶ ሽመልስ፥ አሁን ያለንበት ዘመን የ2ኛ የእድገትና ትራስፎርሜሽን እቅድ ትግበራ የመጨረሻ ዓመት መሆኑን ከግምት በማስገባት በቀሪው ጊዜ ጠንክረው እንደሚሰሩና ጨፌውም አስፈላጊውን ድጋፍ እና ክትትል እንዲያደርግላቸው ጥሪ አቅርበዋል።
ጨፌው ለሁለት ቀናት በሚኖረው ቆይታው የተለያዩ ረቂቅ አዋጆች እና ሹመቶችም ቀርበው ውይይት ከተደረገባቸው በኋላ ይፀድቃሉ ተብሎ ይጠበቃል።
እንዲሁም ጨፌው በመደበኛ ጉባዔው በህግ የበላይነትና የክልሉ የጸጥታ ሁኔታ ላይ በትኩረት እንደሚመክርም ተገልጿል።
በሙለታ መንገሻ
ትኩስ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ገፃችንን ሰብስክራይብ ያድርጉ!
https://t.me/fanatelevision