ቢዝነስ

በኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋያቸውን ማፍሰስ የሚፈልጉ ዳያስፖራዎችን የሚያበረታታ ፎረም ተዘጋጀ

By Alemayehu Geremew

January 05, 2022

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 27፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን እና የአዲስ አበባ ኢንቨስትመንት ቢሮ ጋር በመሆን በሀገሪቱ መዋዕለ ንዋያቸውን ማፍሰስ የሚፈልጉ ዳያስፖራ ባለሀብቶችን የሚያበረታታ እና ግንዛቤ የሚያሳድግ ፎረም አዘጋጁ።

ሁለቱ ተቋማት በጋራ በሠጡት መግለጫ ፎረሙ ጥር 3 ስራ የሚጀምር ሲሆን፥ ጥር 6 ይጠናቀቃል ተብሏል፡፡

ፎረሙ ጥር 3 በይፋዊ የመክፈቻ ሥነ-ሥርዓት እንደሚጀመር እና በቀጣይ ቀናትም የተለያዩ መርሃ ግብሮች እንደሚኖሩት ነው ኮሚሽኑ የገለጸው፡፡

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን፥ ኢትዮጵያ ውስጥ መዋዕለ ንዋያቸውን የማፍሰስ ዕቅድ ያላቸው ዳያስፖራ ባለሐብቶች በፎረሙ እንዲሳተፉ እና ከኢንቨስትመንት ማኅበረሰቡ፣ ከኮሚሽኑ የፌዴራል እና የክልል እንዲሁም የከተማ አሥተዳደር ኃላፊዎች እና ባለሙያዎች ጋር እንዲመክሩ ብሎም የኢንቨስትመንት አማራጮችን እንዲመለከቱ ነው ጥሪ ያቀረበው፡፡

በኢንቨስትመንት መሰማራት እና በዕድሉ መጠቀም የሚፈልጉ ባለሐብቶች investethio.com የሚለውን የኮሚሽኑን ድረ ገጽ መመልከት እንደሚችሉም ተጠቁሟል፡፡

በፍሬሕይወት ሰፊው