የሀገር ውስጥ ዜና

ተቀዳሚ ሐጂ ሙፍቲ እድሪስና የሥራ ሃላፊዎች በቦረና ድርቅ ያደረሰውን ጉዳት ተመለከቱ

By Alemayehu Geremew

January 05, 2022

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 27፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ እሥልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ሐጂ ሙፍቲ እድሪስ፣ አምሳደሮች እና ከፍተኛ የመንግስት የሥራ ኃላፊዎች በቦረና ዞን የሚገኙ በድርቁ የተጎዱ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ጎብኝተው ድጋፍ አድርገዋል።

ወደ ዞኑ ያቀናው ቡድን በአባ ገዳዎች አቀባበል እንደተደረገለትም ነው የተመለከተው።

ጉዳቱ ከዚህ ቀደም ከደረሱ ጉዳቶች የከፋ መሆኑን የአካባቢው አርሶ አደሮች አስረድተዋል፡፡

ከድርቁ መከሰት ጋር ተያይዞ ለዞኑ የድርቅ አደጋው ተጎጂ የኅብረተሰብ ክፍሎች በተለያዩ አካላት የተደረጉ ድጋፎች በቂ ባይሆኑም ችግሩን በመጠኑም ቢሆን ለማቃለል ያግዘናል ብለዋል አባ ገዳዎች፡፡

አካባቢውን እየጎበኘ ያለው ልዑክ በዱቡሉቅ ወረዳ በመገኘት ANE በተባለ በጎ አድራጊ ድርጅት የተዘጋጀውን 600 ኩንታል የምግብ እህል፣ 20 ሺህ ኪሎ ግራም የተመጣጠነ ምግብ እና 6 ሺህ ሊትር ዘይት ለ1 ሺህ 200 አባወራዎች አስረክቧል።

ድጋፉ ለሦስተኛ ጊዜ እንደተደረገና ጠቅላላ ወጪውም 7 ሚሊዮን ብር መሆኑን ነው የድርጅቱ ዳይሬክተር ሣኅሉ ሱልጣን የተናገሩት፡፡

የቦረና ዞን ዋና አስተዳዳሪ ጃርሶ ቦሩ በድርቅ ለተጎዱ ወገኖች ለተደረገላቸው ድጋፍ ድርጅቱን እና በጎ አድራጊ ግለሠቦችን ማመስገናቸውን የኦሮሚያ ኮሙኒኬሽን ቢሮ መረጃ አመላክቷል፡፡