Fana: At a Speed of Life!

በኤርትራ ላይ የሚጣል ህገ ወጥ ማዕቀብ ተቀባይነት የለውም – የቻይና የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ዋንግ ዪ

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 27፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የቻይና የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ዋንግ ዪ ከኤርትራ ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ጋር የሀገራቱን የሁለትዮሽ ፍላጎት ያቀራረበ ፍሬያማ ውይይት ማካሄዳቸውን ገለጹ፡፡

ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ በቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የተመራውን ከፍተኛ ልኡካን ቡድን በጽኅፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል፡፡

በውይይታቸው ዋንግ ዪ በኤርትራም ሆነ በሌላ ሀገር ላይ የሚጣል ማንኛውም አይነት የአንድ ወገን ህገ ወጥ ማዕቀብ ተቀባይነት እንደሌለው አስምረውበታ ነው የተባለው፡፡
የኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ፥ በቻይና ኮሙዩኒስት ፓርቲ የ100 ዓመታት የመሪነት ቆይታ ቻይና እና የቻይና ህዝብ በበርካታ ዘርፍ ያስመዘገቧቸውን ዕድገት ማድነቃቸውም ተመልክቷል፡፡

ለተቀረው የዓለም ክፍልም ቻይና ትልቅ ምሳሌ ትሆናለች ማለታቸው ተጠቁሟል፡፡

ቻይና ዓለም አቀፍ ህግን በማክበር ሚዛናዊ የሆነ ዓለም አቀፋዊ ሥርዓት ዕውን እንዲሆን ላበረከተችው ጉልህ ሚናም የኤርትራው ፕሬዚዳንት እውቅና ሰጥተው ማመስገናቸው ነው የተመለከተው፡፡

የኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ በሀገራቸው የልማት ዕቅድ እና ፕሮግራም ላይ እንዲሁም በቀጣናዊ እና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች ላይ ለቻይናው የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ገለጻ አድርገዋል፡፡

የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት ማጠናከር እንደሚፈልጉም ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ጠቁመዋል፡፡

የቻይና የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ዋንግ ዪ፥ ፕሬዚዳንት ሺ ጂንፒንግ ከኤርትራ ጋር የሁለትዮሽ እስትራቴጂያዊ ግንኙነታቸውን ለማጠናከር እንደሚፈልጉ እና በጉዳዩ ላይ በጥልቀት ለመምከርም ቻይናን እንዲጎበኙ ለፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ የግብዣ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡

ሀገራቱ በቀጣይ በሰው ኃይል እና አቅም ግንባታ፣ በመሠረተ-ልማት ዝርጋታ እንዲሁም በማዕድን እና በምጽዋና አሰብ ወደብ ልማቶች ዘርፍ ላይ ትብብራቸውን ለማጠናከር እና ለማልማት መስማማታቸውን ከኤርትራ ማስታወቂያ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.