Fana: At a Speed of Life!

በሰሜን ወሎ ዞን አሸባሪው ህወሓት የ777 የመጀመሪያ ደረጃ ት/ቤቶችን ቁሳቁስ አውድሟል

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 27፣ 2014 ( ኤፍ ቢ ሲ) አሸባሪው ህወሓት በሰሜን ወሎ ዞን የሚገኙ 777 የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን የመማሪያ ቁሳቁስ ማውደሙን የዞኑ አስተዳደር ገለጸ፡፡

የሰሜን ወሎ ዞን ምክትል አስተዳዳሪ አቶ ጋሻው አስማሜ፥ በዞኑ ስለደረሰው ውድመት እና ሌሎች ጉዳዮች ለመገናኛ ብዙሃን መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫቸውም የሽብር ቡድኑ ህወሓት ታሪክ ይቅር የማይለው በደል በአማራ ህዝብ ላይ መፈፀሙን ተናግረዋል።

የሽብር ቡድኑ በወረራ በቆየባቸው አካባቢዎች የህዝብ መገልገያ ተቋማትን፣ የአስተዳደር ቢሮዎችን፣ ሆስፒታሎች እና የግለሰብ ሃብት እና ንብረቶች ዘርፏል፤ መውሰድ ያልቻለውንም እንዲወድም አድርጓል ብለዋል።

በሌላ በኩል ቡድኑ የሰባት ሆስፒታሎችን ንብረት ከመዝረፍ እና የቤተ ሙከራ መገልገያ መሳሪያዎችን ከማውደሙ ባለፈ በትውልዱ ስነ ልቦና ተፅዕኖ ለማሳደር ትምህር ቤቶችን የጅምላ መቃብር አድርጓል ነው ያሉት፡፡

ህፃናት እና አዛውንቶች በጅምላ ተደፍረዋል፤የግለሰብ አስከሬን አታነሱም እያሉ በህዝቡ ላይ መዘባበታቸውንም ጠቁመዋል፡፡

በሌላ በኩል በዞኑ የሚገኙ ባለሃብቶች ሃብት ንብረታቸውን በመዝረፍ እና በማውደም ዳግም እንዳይነሱ በማድረግ የኢኮኖሚ አቅም እንዳይኖራቸው የአማራን ህዝብ አንገት ለማስደፋት ያልሰሩት ስራ የለም ሲሉ በመግለጫው አንስተዋል።

ቡድኑ ጥንተ መሰረት ያላቸውን ቤተ እምነቶች በከባድ መሳሪያ በመደብደብ ማውደሙም ተገልጿል።

የወደሙ ተቋማትን አገልግሎት ለማስጀመር የተለያዩ ተቋማት ጥረት እያደረጉ እንደሚገኙ ጠቁመው÷ የስልክ እና የኢንተርኔት አገልግሎት ጀምሯል ነው ያሉት።

በዞኑ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ለማስጀመር እየተሰራ እንደሚገኝ እና በከፊል አገልግሎት ያገኙ አካባቢዎች መኖራቸውንም አንስተዋል።

ተፈናቅለው የነበሩ የመንግስት ሰራተኞች ወደ ስራ ቦታቸው እየተመለሱ እንደሚገኙ የገለጹት አቶ ጋሻው÷ መደበኛ የመማር ማስተማር ስራ ለማስጀመር በየደረጃው ምክክር እየተካሄደ መሆኑን ተናግረዋል።

በጤና ተቋማት የጤና ባለሙያዎች በወደሙ የጤና ተቋማት በመሄድ አገልግሎት መስጠት መጀመራቸውንም አንስተዋል።

የዞኑ ህዝቡ ችግር ላይ በመሆኑ ድጋፍ እንደሚያስፈልገው እና ሁሉም ርብርብ እንዲያደርግ ጥሪ አስተላልፈዋል።

በምንይችል አዘዘው

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.