Fana: At a Speed of Life!

ሕዝበ ክርሰቲያኑ የገና በዓልን ሲያከብር የተፈናቀሉ ወገኖችን በመደገፍ ሊሆን እንደሚገባ የኃይማኖት አባቶች ጥሪ አቀረቡ

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 28፣ 2014 ( ኤፍ ቢ ሲ) ሕዝበ ክርሰቲያኑ የኢየሱስ ክርስቶስን የልደት በዓል ሲያከብር የተፈናቀሉ ወገኖችን በመደገፍና ጉዳት የደረሰባቸውን ሐዘናቸውን በመካፈል ሊሆን እንደሚገባ የኃይማኖት አባቶች ጥሪ አቀረቡ።

ኢትዮጵያዊያን ለአገራቸው ሰላም በአንድነት ሊቆሙ እንደሚገባም ነው ያሳሰቡት፡፡

የኃይማኖት አባቶቹ የገና በዓልን ምክንያት በማድረግ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።

በዚህመ መሠረት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ፓትሪያርክ ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ምዕምኑ በዓሉን ሲያከብር የተፈናቀሉ ወገኖችን በማሰብ እንዲሆን ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡

በዓሉን ስናከበር የተራበውን በማብላት፣ የተጠማውን በማጠጣት፣ የታረዘውን በማልበስ እንዲሁም የታመመውንና የታሰረውን በመጠየቅ ሊሆን ይገባል ነው ያሉት።

በተመሳሳይ የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሊቀ ጳጳሳት ካርዲናል ብርሃነየሱስ ሱራፌል፥ የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓልን ስናከብር በጦርነቱ የተፈናቀሉትንና ጉዳት የደረሰባቸውን ወገኖች በማሰብና ሐዘናቸውን በመካፈል ሊሆን ይገባል ብለዋል።

እያንዳንዱ ሰው ወንድምና እህቱን እንደራሱ አድርጎ እንዲወድ ታዟል ያሉት ካርዲናል ብርሃነየሱስ፤ የሰላምን ሰንሰለት ከሚበጥሱት ከትዕቢት፣ ከጥላቻ፣ ከኩራትና ከቁጣ መንፈስ መራቅ እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል፡፡

የኢትዮጵያ ወንጌል አማኞች አብያተ ክርስቲያናት ካውንስል ጠቅላይ ጸሐፊ ቄስ ደረጀ ጀምበሩ በበኩላቸው፥ የገና በዓልን ንብረታቸው ወድሞና ተዘርፎ ቤተሰቦቻቸውን አጥተው በሀዘን ላሉ ወገኖቻችን ፍቅርና አብሮነትን በሚያሳይ መልኩ ማክበር ይገባል ብለዋል።

ስለ ሰላም ማስተማርና መልካም ምሳሌ ሆኖ መገኘት ከክርስቲያኖች የሚጠበቅ በመሆኑ ምዕመናን ራሳቸው ታርቀው የማስታረቅ አገልግሎታቸውን እንዲያከናውኑ ጥሪ ማቅረባቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

በኢትዮጵያ አስተማማኝና ዘላቂ ሰላም ለማስፈን ተቀራርበን መሥራት ይገባናል ያሉት ቄስ ደረጀ፥ በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ አገር ያሉ ኢትዮጵያውያን በአንድነት መቆም እንዳለባቸው ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.