Fana: At a Speed of Life!

ያለ ጥርጥር የኢትዮጵያ ነገ ብሩህ ይሆናል፤ የመከራ ዘመንዋም እስከ ወዲያኛው ይሸኛል – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 29፣ 2014 ( ኤፍ ቢ ሲ) በዚህ ወሳኝ ወቅት ሁላችንም ዐቅማችን የፈቀደውን መሥራት ከቻልን፣ ያለ ጥርጥር የኢትዮጵያ ነገ ብሩህ ይሆናል፤ የመከራ ዘመንዋ እስከ ወዲያኛው ይሸኛል፤ ኢትዮጵያም የማትደፈር፣ የምትታፈር ሀገር ሆና በዐለት ላይ ትቆማለች ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የዘንድሮውን የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል ምክንያት በማድረግ ባስተላለፉት መልዕክት፥ በዓሉን የምናከብረው የመከራችን ዘመን እያከተመ፣ የችግራችን ቋጠሮ እየተፈታ፣ የሰቆቃችን ምንጭ ላይመለስ እየደረቀ ባለበት ወቅት ነው ብለዋል።

ጁንታው መከላከያ ሠራዊታችን ላይ የፈጸመውን ጥቃት ተከትሎ ባለፈው አንድ ዓመት ውስጥ የተፈጠረውን ግጭት ጨምሮ በሌሎች ምክንያቶች በሀገራችን የተፈጸሙ መበዳደሎችን ለመሻር በዚህ ሰዓት ሀገራዊ እርቀ ሰላም እንደሚያስፈልግም ጠቁመዋል።

አንድነታችንን ለማስጠበቅ ስለሚያስችለን፣ በእርቀ ሰላሙ ኢትዮጵያ አትራፊ እንደምትሆን እሙን ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፥ በሰውና በፈጣሪ እርቅ ምክንያት የከሠረው አሳሳቹ ዲያብሎስ እንደሆነው ሁሉ፣ በሀገራችን እርቀ ሰላም ምክንያት የሽብር ቡድኖቹ የሕወሃትና የሸኔ እኩይ ዓላማ፣ እንዲሁም የታሪካዊ ጠላቶቻችን ሕልም እንደሚከሽፍ አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ጠላቶች ሊወለድ ያለውን ተስፋችንን ሊያጨነግፉ ለዓመታት መታገላቸውን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፥ ተስፋችን መወለዱን ሲያውቁም ያልፈጸሙት የግፍ ዓይነት እንደሌለ አስረድተዋል።

ግጭቶችን እየጠመቁ ሕዝብን ከሕዝብ ሲያጋጩ፣ በየደረሱበት ንጹሐንን ሲያፈናቅሉና ከሕጻናት እስከ አዛውንት ያገኙትን ሲያሰቃዩና በጭካኔ ሲገድሉ እንደነበርም አውስተዋል።

እንደ ሄሮድስ ያሉ አበጋዞች ብሩህ ተስፋችንን ሊያጨልሙ፣ አንድነታችንን ሊንዱ ጥረት ማድረጋቸውን ጠቁመው፥ ሀገራችን ኢትዮጵያ በዚያ ሁሉ መከራ ውስጥ አልፋ እዚህ ደርሳለች ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በበዓል መልዕክታቸው እንደገለጹት፥ የተረገዘው የለውጥ ጽንስ ተወልዶ እያደገ ነው። ኢትዮጵያም በሚወረወሩባት ፍላጻዎች ድልድዮችን እየገነባች፣ ተስፋዋን ለመፈጸም ከመጓዝ ያገዳት የለም።

አክለውም ሀገራችንን ከጥገኝነት የሚያላቅቅ፣ ወገናችንን ከድህነት አዙሪት የሚገላግል፣ ኢትዮጵያን ወደ ብልጽግና ጎዳና የሚያስገባ፣ ኢትዮጵያ ራሷን በሁሉም ነገር ችላ እንድትቆም የሚያደርግ፣ ቁም ነገር ሠርተን ማለፍ አለብን ነው ያሉት።

አሁን የምንገኝበት ወቅት ከትውልድ ወደ ትውልድ ሊሸጋገር የሚችል አንጸባራቂ ገድል የሚሠራበት፣ በኩራት የሚነገር ታሪክ የሚጻፍበት ወሳኝ ወቅት መሆኑንም አስገንዝበዋል።

ማህበራዊ እሴቶቻችን በይቅርታ እየታሹ፣ በእርቀ ሰላም ተጠግነው ወደ ቦታቸው እንደሚመለሱም ነው የገለጹት።

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.