Fana: At a Speed of Life!

“ጀግና ሕዝብ – በቀኝ እጁ ድልን የሚጨብጥ፣ በግራ እጁ ይቅርታና ምህረትን የሚቸር ነው!” – ጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድ

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 29፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ)ጀግና ሕዝብ – በቀኝ እጁ ድልን የሚጨብጥ፣ በግራ እጁ ይቅርታና ምህረትን የሚቸር ነው ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ገለጹ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው የሚከተለውን መልእክት አስተላልፈዋል፡-

“ጀግና ሕዝብ – በቀኝ እጁ ድልን የሚጨብጥ፣ በግራ እጁ ይቅርታና ምህረትን የሚቸር ነው!”

ማንኛውም ጉዞ በስኬት ተቋጨ የሚባለው አንድም በየምእራፉ፣ ሁለትም የጉዞው መጨረሻ በስኬት መጠናቀቅ ሲችል ነው። አጠቃላይ ጉዞው ያማረና የሠመረ እንዲሆን እያንዳንዱ ምእራፍ በሚገባ መቋጨት አለበት። የቤቱ ጥንካሬና ውበት የሚመሠረተው ቤቱን ከገነቡት እያንዳንዱ ጡብዎች ጥንካሬና ውበት እንጂ፣ በጣራው ጥንካሬና በግድግዳ ቀለም ብቻ አይደለም። በያንዳንዱ እርከን ውበቱና ጥንካሬው እየተረጋገጠ የመጣ ቤትም፣ በግንባታው መጨረሻ – በድምድማቱ አምሮና ጠንክሮ መቋጨት አለበት። እንዲያ ሲሆን ቤቱ – እድሜው ረጅም፣ ሲኖሩበት የሚያምር ይሆናል፡፡ በሀገራችን ባህል የጋቢ ወይም የነጠላ መጨረሻው መቋጨት ነው። ያልተቋጨ ነጠላ ወይም ጋቢ የመተርተር ዕድሉ ሰፊ ነው።

የሀገራችን ጉዞ በተደጋጋሚ ከሚገጥመው ፈተና አንዱ በተገቢ መንገድ ምእራፎቹንም ሆነ ፍጻሜውን ያለመቋጨት ነው። በዚህ የተነሣም በሂደቱ የተገኙ ድሎች በየምእራፉ ሲዝረከረኩ ይገኛሉ፤ ወይም የታሰበላቸውን የፍጻሜ ውጤት ሳያመጡ ይቀራሉ። ማንኛውም ሀገራዊ ተግባር መለካት ያለበት በሂደቱና በውጤቱ ነው። ሂደቱም ውጤቱም ተገቢውን ደረጃ ጠብቀው ተገቢን ውጤት ማምጣት አለባቸው።

ሀገራዊ ለውጡን ከጀመርን ጊዜ አንስቶ “መንገዳችን መደመር፣ ግባችን ብልጽግና ነው” ብለናል። በመደመር መንገድ ተጉዘን ወደ ሁለንተናዊ ብልጽግና ለመድረስ ደግሞ ሰላም፣ ይቅርታና ፍቅር (ሰ.ይ.ፍ) ዋናዎቹ
ዕሴቶቻችን መሆናቸውን ገልጠናል። ሀገራዊ ሰላምን ለማስፈን ሰላማዊ የፖለቲካ መንገድን ብቻ መከተል፤ ያለፉ ቁርሾዎችን በይቅርታ መፍታት፤ የወደፊቱን መንገድ ደግሞ በሕዝቦች ፍቅር ላይ በመመሥረት ኅብረ ብሔራዊ አንድነታችንን ማጽናት አለብን ማለታችን ነው።

ከመነሻችን በዋና ዋና ልዩነቶቻችን ላይ ሀገራዊ ምክክር እናድርግ፤ ልዩነቶቻችን በውይይት እንጂ በጠብና በጦርነት አይፈቱም ስንል የነበረው በዚህ የጸና መርሐችን የተነሣ ነው።

ባለፉት ሦስት ዓመታት ከፍቅር ይልቅ ጠብና ጥላቻን በመረጡ፤ ከሰላም ይልቅ የጦርነትን መንገድ በተከተሉ፤ ከይቅርታ ይልቅ ነባር ቁርሾዎችን ለፖለቲካ ትግል መጠቀም በሚፈልጉ ኃይሎች ቀውስ ተፈጥሮብናል። ይሄም ቢሆን እነዚህን ችግሮች ለመፍታት ሰላማዊውን መንገድ መርጠን ነበር። ነገር ግን እነዚህ ከጥላቻና ከጦርነት፣ ከጠብና ከመከፋፈል ውጭ ህልውና የሌላቸው አካላት ሰላማዊውን መንገድ አልመረጡም። የዘረጋናቸውን የሰላም እጆች ነክሰዋል። ከእኛ ይቅር በሚል መርህ ግማሽ መንገድ ስንቀርባቸው እጥፉን እየሸሹ፣ ልዩነቶች በሰላማዊ መፍትሔ ሊታረቁ ሲችሉ የጸብ መንደር ውስጥ ይዘውን ገብተዋል።

ሀገራችን ከአንድ ዓመት በላይ ከአሸባሪዎቹ ሕወሐትና ከጋሻ ጃግሬው ሸኔ ጋር ጦርነት የገባችው፣ የዘረጋነውን የሰላም እጅ ረግጠው ጦር ስለመዘዙብን ነው። መንግሥት የመጀመሪያ ምርጫው ምንጊዜም ችግሮችን በሠለጠነ መንገድ ለመፍታት ነው። ሰላማዊ መንገድ አድካሚና አታካች ቢመስልም ሰብአዊና ቁሳዊ ጉዳትን በከፍተኛ
ሁኔታ ይቀንሳል። ለጦርነት ሊውል የሚችለውን የሰው ኃይልና በጀትም ለብልጽግና ለማዋል ያስችላል። ዳሩ ግን ሰላም በአንድ ወገን ፍላጎት ብቻ የሚገኝ አልሆነም። የቱንም ያህል ብንታገስ፣ የቱንም ያህል ለሰላም ደፋ ቀና ብንል የጠላት ልብ ደነደነ እንጂ አልተለወጠም።

ማንኛውም የሰላም፣ የይቅርታና የፍቅር መንገድ ሊጥሳቸው የማይገቡ ቀይ መሥመሮች አሉ። ኅብረ ብሔራዊ አንድነታችንን የሚከፋፈል፣ የሀገራችንን ክብርና ሉዓላዊነት የሚጥስና የግዛት አንድነታችንን ለአደጋ የሚያጋልጥ ማንኛውንም መፍትሔ ተቀባይነት የለውም። የክህደትና የክፍፍል መንገድን የሚከጅል ሁሉ፣ የኢትዮጵያውያን ክንድ መቅመሱ አይቀርም። ከዚያ በታች ባሉ ጉዳዮች ዙሪያ ችግሮችን በጠረጴዛ ዙሪያ ለመፍታት ድሮም ልባችን ክፍት ነበር፤ ወደፊትም የሰላም እጃችን አይታጠፍም፡፡

ከአሸባሪው ሕወሐትና ከተላላኪው ሸኔ ጋር ያደረግነው ጦርነት ቀይ መሥመሩ በመጣሱ ምክንያት የተከሠተ ነው። አሸባሪወው ሕወሐት ኅብረ ብሔራዊ አንድነታችንን ለመከፋፈል ተነሣ፤ የሀገራችንን ክብርና ሉዓላዊነት ከባዕዳን ጋር ሆኖ ለመግሠሥ ጦሩን ሰብቆ ሰሜን ዕዝን አጠቃ፤ የግዛት አንድነታችንን ለአደጋ እንዲጋለጥ በር ከፈተ። የቅርብና የሩቅ ጠላቶቻችንም እንደ ፈለጉት እጃችንን ሊጠመዝዙ ምክንያት አገኙ። በሀሰት ፕሮፓጋንዳቸውና ሴራ ባልተለየው የሚዲያ ዘመቻዎቻቸው ኢትዮጵያን በማዋከብ የፍላጎታቸው ተንበርካኪ ሊያደርጓት ሌት-ተቀን ይሮጡ ጀመር።

የጥንካሬና የኩራታችን ምንጭ የሆነው ሕዝባችን ግን በቀላሉ የሚበገር አልሆነም። በሀገር ውስጥ አሸባሪም ሆነ በውጭ ኃይሎች ሉአላዊነቱ ተነክቶበት ሕዝባችን እጁን አጣጥፎ አልተቀመጠም። ቀፎው እንደተነካ ንብ ‹ሆ› ብሎ በመነሳት በሁለት አቅጣጫ የተሰነዘረበትን ጥቃት በብቃት እየመከተ ይገኛል።

ጀግና ሕዝብ ለጭቆና መንበርከክን እንጂ ትህትናና ይቅርታን አይጠላም። አሸናፊ – ድል አጥባቂ፣ ትኁት እና መሐሪ ነው። ሕዝባችን “ውጊያ የሰው፣ ድል የፈጣሪ ነው” ብሎ ያምናል። አሁን ያገኘነውን ድል በሦስቱ የኢትዮጵያውያን የድል ዕሴቶች ብንቋጫቸው መልካም ነው። ድልን በማጥበቅ፣ በትኅትና እና በምሕረት። አሁን ያገኘነውን ድል እንዳይቀለበስ አድርገን በሁሉም መስክ በሩን ሁሉ ማጥበቅ አለብን። በኢትዮጵያዊ ትኅትና ደግሞ አሁን የገጠምነው ጦርነት በሰላም መንገድ እንዲጠናቀቅ እናደርጋለን። በአንድ በኩል ድል አድራጊውን የኢትዮጵያ ክንድ እያሳየን፣ በሌላ በኩል ደግሞ ትኁቱን የኢትዮጵያውያን ልብ እናሳያለን። በድል አድራጊ የኢትዮጵያ ክንድ ጠላቶቻችን አፈር ልሰው እንዳይነሡ እንመክታለን። በትኁቱ የኢትዮጵያ ልብ ከፉከራና ኩራታችን ቀንሰን ዛሬም ለሰላም በራችን ክፍት መሆኑን እንናገራለን። ጦርነት ውስጥ የገባነው ሰላምን በሌላ በምንም መልኩ ለማምጣት ስላልቻልን ነው። ጦርነት ሰላምን የማረጋገጫ የመጨረሻው አማራጭ ነውና።

ከጦርነት ወደ ሰላም ለመምጣት ያልቻሉ ኃይሎችን ወደ ሰላም ጠረጴዛ የምናመጣበት የመጨረሻ ጉልበት ነው።በባህላችንም የግጭት መቋጫው ዕርቅና ይቅርታ ነው። ደም የተቃቡ ጠበኞችን ጭምር እስከማጋባት የሚደርስ የዕርቅና የሰላም ዕሴት ያለን ሕዝቦች ነን።

ኢትዮጵያዊ ድል አድራጊነት ምህረትንም ያውቃል። በአድዋ ጦርነት የተማረኩትን የጣልያን ወታደሮች በአሸናፊ ምሕረት ምረናል። በዚህም ጣልያኖች ራሳቸው ተገርመው በሰልፍ እስከ ማመስገን ደርሰው ነበር። ያ ታላቅ ኢትዮጵያዊ ዕሴት ነው። ዛሬም ኢትዮጵያ በአሸናፊነት ክብር ላይ ናት። ፍትሕ ያልተለየው ምሕረትን አብሮ በማስኬድ ኢትዮጵያ እንድታሸንፍ እናደርጋለን። በአንድ በኩል በደልና ጥፋትን በፍትሕ መንገድ እያየን፣ በሌላ በኩል ለእርምትና ለይቅርታ ቦታ በመስጠት የምሕረትን መንገድ መከተል አለብን።

ከድላችን ማግሥት አራት ነገሮችን መርሖቻችን አድርገን እንሄድባቸዋለን። 1ኛ – ድላችንን እንዳይቀለበስ አድርገን በሁለንተናዊ መስክ እናጠብቀዋለን። 2ኛ – ድላችን ዘላቂ እንዲሆን በፖለቲካዊና ሰላማዊ መንገዶች እንዲቋጭ እናደርገዋለን። 3ኛ – ድላችንን ለመጠበቅና ድላችን ዘላቂ ለማድረግ እንድንችል በአሸናፊ ምሕረት ግጭቱ
የፈጠረውን ውጥረት እናረግባለን። 4ኛ – ያጠፋ እንዲቀጣ፣ የበደለ እንዲክስ የሚያደርግ ሁሉን አቀፍ ፍትሕ በሽግርር እና በተሃድሶ ፍትህ እይታ፣ ሃገራዊ ባህሎቻችን እና አሴቶቻችን ታሳቢ ባደረገ መልኩ ፍትህ እናሰፍናለን። እነዚህ አራቱ መርሖች አንዱ ሌላውን ሳይተካ ሁላችንንም አሸናፊ በሚያደርግ መልኩ እንደ አስፈላጊነታቸው ሁሉንም እንተገብራለን።

በድል፣ በምሕረትና በትኅትና፣ ኢትዮጵያን ዘላቂና የጸናች አሸናፊ እናደርጋታለን።

ኢትዮጵያ በልጆቿ ጥረት ታፍራና ተከብራ ለዘላለም ትኑር!!
ፈጣሪ ኢትዮጵያና ሕዝቦቿን ይባርክ!
ታኅሣሥ 29 ቀን 2014 ዓ.ም.

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.