ፖምፔዮ የአፍሪካ ሃገራት የስራ እድል ፈጠራን ለማሳደግ የግሉን ዘርፍ ማጠናከር እንደሚገባቸው ተናገሩ
አዲስ አበባ ፣ የካቲት 11 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማይክ ፖምፔዮ የአፍሪካ ሃገራት የስራ እድል ፈጠራን ለማሳደግ የግሉን ዘርፍ ማጠናከር እንደሚገባቸው ተናገሩ።
በአፍሪካ የስራ እድል ፈጠራ እና በአህጉራዊ ምጣኔ ሃብት ላይ ትኩረት ያደረገ መድረክ ተካሄዷል።
የአፍሪካን ስራ ፈጣሪዎች ነጻ ማውጣት በሚል መሪ ቃል በተመድ የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን አዳራሽ በተካሄደው መድረክ ላይ፥ ማይክ ፖምፔዮ መልዕክት አስተላልፈዋል።
በመልዕክታቸውም የኢኮኖሚ ነጻነት ያለውን ፋይዳ በተመለከተ ገለጻ አድርገዋል።
በዚህ ወቅትም የግሉን ዘርፍ ማጠናከር የስራ እድል ፈጠራን ለማሳደግና ብልፅግናን ለማረጋገጥ ወሳኝ መሆኑንም አጽንኦት ሰጥተዋል።
ከዚህ ባለፈም የተረጋጋ እና ከሙስና የፀዳ ከባቢ መፍጠር የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ አይነተኛ ሚና እንዳለው ጠቅሰዋል።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እየተካሄደ ያለውን ማሻሻያ ያደነቁት ፖምፔዮ፥ የፕሬዚዳንት ትራምፕ አስተዳደር የአሜሪካን እና የአፍሪካን የንግድ ትስስር የማጠናከር ፍላጎት እንዳለውም ገልጸዋል።
ዋሽንግተን ለአፍሪካ ሃገራት በሰጠችው ከታሪፍና ከኮታ ነጻ የገበያ እድል በርካታ ሃገራት ተጠቃሚ መሆናቸውን የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት አስታውቋል።
በዚህም ኢትዮጵያ ባለፉት አመታት ወደ አሜሪካ ገበያ የምትልካቸው ምርቶች እየጨመረ የመጣ ሲሆን፥ በዚህም የሁለቱ ሃገራት የጋራ ተጠቃሚነት ተረጋግጧል ነው ያለው።
በፈረንጆቹ 2018 በሃገራቱ መካከል የ1 ነጥብ 8 ቢሊየን ዶላር የንግድ ልውውጥ የተካሄደ ሲሆን፥ ከዚህ ውስጥ ኢትዮጵያ 1 ነጥብ 3 ቢሊየን ዶላር ዋጋ ያላቸውን ሸቀጦች ወደ አሜሪካ ልካለች።
በተጨማሪም አሜሪካ 445 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር ዋጋ ያላቸውን ምርቶች ወደ ኢትዮጵያ ልካለች።
ከዚህ ባለፈም የአሜሪካ መንግስት ለኢትዮጵያ የተለያዩ ድጋፎችን እያደረገ ይገኛል።
ከዚህ ውስጥ በኢትዮጵያ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን ለማሳደግ፣ የንግድ ድባቡን ለማሻሻል፣ ለባለሃብቶች ምቹ መደላድል ለመፍጠር፣ የስራ እድል ፈጠራን እና በኢትዮጵያ የሚያደርገውን ኢንቨስትመንት ለማበረታታት ከ117 ሚሊየን ዶላር በላይ መድቧል።
እንዲሁም ለኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ከ37 ሚሊየን ዶላር በላይ ድጋፍ አድርጓል።
ድጋፉ የቦርዱን ተዓማኒነት ለማሳደግና የሲቪል ማህበረሰብ አባላትን እና የህብረተሰቡን ተሳትፎ ለማሳደግ የሚረዳ ነው ተብሏል።
ትኩስ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ገፃችንን ሰብስክራይብ ያድርጉ!
https://t.me/fanatelevision